አስፈላጊውን የኮቪድ-19 ጥንቃቄ በማድረግ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እንደሚጀመሩ ተጠቆመ

62

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13/2013 ( ኢዜአ) አስፈላጊውን የኮሮናቫይረስ  ጥንቃቄ በማድረግ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እንደሚጀመሩ የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን አስታወቀ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውሳኔዎችን ማሳለፉ ይታወቃል።

በዚህም ወረርሽኙን በመከላከልና አስፈላጊ ጥንቃቄዎችን በማድረግ ተቋርጠው የነበሩ ስፖርታዊ ውድድሮችን ማስጀመር የሚለው ከተላለፉት ውሳኔዎች መካከል ይገኝበታል።

በስፖርታዊ እንቅስቃሴ አጀማመር ዙሪያ መግለጫ የሰጡት የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዱቤ ጅሎ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በአጠቃላይ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ መደረጉን አስታውሰዋል።

ይህንንም ተከትሎ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን በመውሰድና የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ መሠረት በማድረግ ኮሚሽኑ ረቂቅ መመሪያ አዘጋጅቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ማድረጉን ገልጸዋል።

ከውይይቱ በኋላ ለሚመለከተው አካል ቀርቦ ፈቃድ እንዲሰጥ መደረጉን ተናግረው፤ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ መወሰኑን አመልክተዋል።

በዚህም ስልጠናዎችና ውድድሮች ከመጀመራቸው በፊት በሰው ሀይል፣ ወረርሽኙን መከላከል በሚያስችል ግብዓት፣ በማዘውተሪያ ስፍራዎችና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ያለውን ዝግጁነት ማረጋገጥ ቅድሚያ እንደተሰጠው ጠቅሰዋል።

ውድድር ላይ የሚካፈሉ ስፖርተኞችም ወደ ሆቴል ከመግባታቸው አስቀድሞ ምርመራ የሚያደርጉ መሆኑንም አቶ ዱቤ ተናግረዋል።

የወረርሽኙ ሁኔታ እየታየ የተወሰነ ተመልካች እንዲገባ የሚደረግ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ዱቤ አሁን የሚጀመሩ ውድድሮች በዝግ ስታዲየም ያለ ተመልካች እንደሚካሄዱ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ስታዲየምን በተጠናከረ ሁኔታ እድሳት ተደርጎለት ለውድድር ዝግጁ እንዲሆን ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ነው የገለጹት።

እያንዳንድ የስፖርት ማህበራትም በኮሚሽኑ እና በጤና ሚኒስቴር የወጣውን መመሪያ ተከትለው እንዲሰሩ መመሪያ የተሰጠ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ለዚህም በአገር አቀፍና በክልሎች ደረጃ ስራውን የሚመራና የሚከታተል የጤናና የጸጥታ ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋሙን ገልጸው፤ መመሪያውን ተላልፎ የሚገኝ አካል ላይ አስፈላጊው እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም