በጌዴኦ ዞን አመራሮች ደም ለገሱ

118

ዲላ መስከረም 13/2013 (ኢዜአ) በዲላ ከተማ በስልጠና ላይ የሚገኙ የጌዴኦ ዞን የብልፅግና ፓርቲ መካከለኛ አመራሮች ደም ለገሱ።

ከአመራሮቹ  መካከል አቶ ክብሩይስፋው ወጋየው ከስልጠናው ጎን ለጎን በደም ልገሳ መረሃ ግብሩ በመሳተፍ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

እናት ሕይወት እየሰጠች ሕይወቷን ማጣት የለባትም በሚል መርህ ደም ለሚያስፈልጋቸው  ወገኖች ደም በመለገሳቸው ደስተኛ እንደሆኑ  ተናግረዋል።

አመራሩም የተጣለበትን ኃላፊነት በብቃት ከመወጣት ባለፈ በበጎ ተግባራት ላይ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ለሌሎች አርአያ መሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በተለያየ ህመም ውስጥ ሆነው በደም እጦት የሚቸገሩ ወገኖችን ለመርዳት ደም መለገሳቸውን የገለጹት ሌላው የስልጠናው ተሳታፊ አቶ መልካሙ ሽፈራው ናቸው።

በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ደም በመለገስ ሁሉም አካል በተለይም አመራሩ ግንባር ቀደም ኃላፊነቱን ሊወጣ  እንደሚገባም አመልክተዋል።

አቶ እድሉ ታደሰ በበኩላቸው በመረሃ ግብሩ በመሳተፍ ለአምስተኛ ጊዜ ደም መለገሳቸውን ተናግረዋል።

በዞኑ ያለውን የደም እጥረት ችግር ለማቃለል ሁሉም አካል  መሳተፍ እንዳለበትም ጠቁመዋል።

በተያዘው ወር በጌዴኦ ዞን  ከ208 ዩኒት በላይ ደም ለመሰብሰብ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የዲላ ደም ባንክ ኃላፊ ሲስተር መስከረም ዘውዴ ናቸው።

ሆኖም ትምህርት ቤቶችና መሰል ህዝብ የሚበዛባቸው ተቋማት መዘጋታቸውን ተከትሎ በዞኑ በየወሩ የሚታቀዱ የደም መጠን ለማሳካት ማዳገቱን  ጠቅሰዋል።

ችግሩን ለማቃለል በስልጠና ተሳታፊ የሆኑ አመራሮች በደም ልገሳው እንዲሳተፉ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም