የውጭ ባለሀብቶችን በቱሪዝም ኢንቨስትመንት በማሳተፍ ዘርፉን ለማሳደግ እየተሰራ ነው

58

ጎንደር፣ መስከረም 13/2013 (ኢዜአ) የተሻለ ልምድ ያካበቱ የውጭ ባለሃብቶችን በክልሉ የቱሪዝም ኢንቨስትመንት በማሳተፍ ዘርፉን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ፡፡

የሱዳን ባለሃብቶችንና የንግዱ ማህበረሰብ አባላትን ያቀፈ የልኡካን ቡድን በጎንደርና አካባቢው የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎችን መጎብኘት ጀምሯል።

የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ሙሉቀን አዳነ እንደተናገሩት ክልሉ ለቱሪዝም ኢንቨስትመንት አመቺ የሆኑ በቁጥር የበዙ መዳረሻ ስፍራዎች ቢኖሩም በዘርፉ የተሰማሩ የውጭ ባለሃብቶች ተሳትፎ ዝቅተኛ ነው፡፡

ክልሉ በቱሪዝም ኢንቨስትመንት ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸውን ባለሃብቶች ለመሳብ በውጭ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም የሱዳን ባለሃብቶች በክልሉ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን እንዲጎበኙ በማድረግ በቱሪዝም ዘርፍ መዋለ ንዋያቸውን ማፍሰስ እንዲችሉ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በክልሉ የቱሪስት ፍሰት ሊያስተናግዱ የሚችሉ አለምቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎችና መዝናኛ ስፍራዎች እንደሚያስፈልጉ ጠቅሰው፤ በዚህ ረገድ የውጭ ባለሃብቶች ተሳትፎ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ ብቁና የሰለጠነ የሰው ኃይል፤ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት፤ የዳበረ እውቀትና ቴክኖሎጂ ጭምር የሚጠይቅ በመሆኑ የውጭ ባለሃብቶችን በስፋት ማስተዋወቅና መሳብ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

የክልሉ መንግስት በቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች መንገድ፣ መብራት፣ ውሃና ሌሎችም መሰረተ ልማቶችን በማሟላት ለውጭ ባለሀብቶች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ይሰራል ብለዋል።

ለቱሪዝም ኢንቨስትመንት መስፋፋትና ማደግ የሰላምና ደህንነት ጉዳይ ቁልፍ አጀንዳ እንደሆነ የጠቆሙት ዶክተር ሙሉቀን ፤  ዘላቂ ሰላም እንዲኖር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የጎንደር ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ተሾመ አግማስ በበኩላቸው የውጭ ባለሃብቶች በቱሪዝም ኢንቨስትመንት ተሳታፊ እንዲሆኑ የተጀመረው እንቅስቃሴ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የተቀዛቀዘውን ለማነቃቃት የጎላ ድርሻ አለው ብለዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ለውጭ ባለሃብቶች መሰረተ ልማት የተሟላላቸው የኢንቨስትመንት ቦታዎችን ከማዘጋጀት ጀምሮ ቀልጣፋ መስተንግዶ ለመስጠት በዝግጅት ላይ  እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያና ሱዳን ዘመናትን የዘለቀ የንግድና የባህል ትሰስር ያላቸው ሃገሮች ናቸው ያሉት ደግሞ የሱዳን ልኡካን ቡድን አባልና ባለሃብት የሆኑት ኢንጂነር ኡመር ኢብራሂም ናቸው። 

የልኡካን ቡድኑ አባላት በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር እንዲኖር በማድረግ አመቺ በሆኑ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ የመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸውም ገልፀዋል።

በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ይበልጣል አእምሮ በበኩላቸው ኢትዮጵያና ሱዳን ከህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ጀምሮ በንግድና በመሰረተ ልማት የተሳሰሩ ወንድማማች ህዝቦች ናቸው ብለዋል፡፡

የሱዳን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በቱሪዝምና ኢንዱስትሪው ዘርፍ መዋለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ፍላጎት ማሳየታቸውን ጠቅሰው፤ የልኡካን ቡድኑ አመጣጥም የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አማራጮች ተመልክቶ ለመወሰን መሆኑን ተናግረዋል።

በትናንትናው ዕለት ጎንደር ከተማ የገባው የሱዳን ባለሃብቶችና ንግዱ ማህበረሰብ አባላት የያዘው ልኡካን ዛሬ የሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክንና በጣና ሃይቅ ዳርቻ የምትገኘውን የጎርጎራ ከተማ መጎብኘት ጀምሯል።

22 አባላት ያሉት ልኡካኑ በቀጣዮቹ ቀናትም በኦሮሚያ፣ ደቡብና አፋር ክልሎች የኢንቨስትመንት አማራጮች ምልከታ እንደሚያደርጉም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም