የመተከል አመራር መዋቅር በአዲስ የመተካት ግምገማ ተጀመረ

64

አሶሳ መስከረም 13/2013 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የአመራር መዋቅር የማስተካከያ ግምገማ ዛሬ ግልገልበለስ ከተማ ተጀመረ፡፡

የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ በየነ ለኢዜአ እንደተናገሩት ግምገማው በመተከል ዞን ግጭት የተከሰተባቸውን ጉባ ፣ ወምበራ ፣ ቡለን፣ ዳንጉር፣ ፓዌ እና ድባጤ ወረዳዎች አመራሮች ላይ ያተኩራል፡፡

ለሁለት ቀናት የሚቆየው የግምገማ መድረኩ የሚመራው  በክልሉ ከፍተኛ አመራሮች መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በግምገማው በተለይ ግጭቱ በተከሰተባቸው ወረዳዎች አመራሮችን ከኃላፊነት ከማንሳት ባሻገር በተጨባጭ መረጃ በመመርኮዝ በህግ ተጠያቂ እስከ ማድረግ ውሳኔ ላይ ይደረሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል፡፡

በመተከል ዞን ከሐምሌ 2012 ዓ.ም ጀምሮ በተለያየ ጊዜ በተከሰተው ግጭት የተጠረጠሩ  328 ግለሰቦች  በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ቀደም ሲል ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም