ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ለፀጥታና ደህንነት አካላት የፀረ-ሽብር ሥልጠና ሰጠ

86

አዲስ አበባ፣ መስከረም 13/2013 ( ኢዜአ) ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ለፀጥታና ደህንነት አካላት ሽብርተኝነትን መከላከልና ማክሸፍ በሚያስችሉ ስልቶች ላይ ያጠነጠነ ስልጠና መስጠቱን ገልጿል።

ስልጠናው ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ ከፌዴራልና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽኖች፣ ከሪፐብሊካን ጋርድና ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ልዩ ኃይል ለተውጣጡ አመራሮችና አባላት ነው የተሰጠው።

ሽብርተኝነትን መከላከልና ማክሸፍ፤ የሽብር ተልዕኮዎችንም አስቀድሞ ማወቅ የሚቻልበትን የመረጃ ሥራ በተመለከተ የንድፈ ሃሳብና የተግባር ሥልጠና ነው።

አል ቃይዳ፣ አይ.ኤስ እና አልሸባብ የሽብር ቡድኖች የኢትዮጵያና የአካባቢውን አገራት የሠላም፣ የትብብርና የልማት ማዕቀፍ ለማደናቀፍ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ለመግታትና ለማክሸፍ ያለመ ስልጠና መሆኑም ተገልጿል።

ሽብርተኝነት የደቀነውን ስጋት፤ አሸባሪዎች የሚጠቀሙበትን ስልት እንዲሁም የቀጣናውንና ዓለም አቀፋዊውን ነባራዊ ሁኔታ የዳሰሰ ሲሆን፤ ስጋቱን መመከት የሚያስችሉ ንድፈ ሃሳባዊና ተግባራዊ የመከላከያ ዘዴዎችንም አካቷል።

የሽብር ጥቃቶች ቢፈጸሙ በቀላሉና በአነስተኛ ኪሳራ ማክሸፍ በሚያስችል ስልት ላይ ያተኮረ መሆኑም ተመልክቷል።

የስልጠናው ተሳታፊዎች ከስልጠናው ዓለም አቀፋዊ ሽብርተኞች የሚጠቀሙባቸውን ስልቶች እንዴት መከላከል እንደሚቻል ግንዛቤ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

በምስራቅ አፍሪካ አካባቢ የሚንቀሳቀሱ የሽብር ቡድኖች በኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ላይ ጉዳት ለማስከተል የሚሸርቡትን ሴራ ለማክሸፍ እንደሚያግዝም ተሳታፊዎቹ ጨምረው ገልጸዋል።

የፀጥታና የደህንነት አካላቱ ተቀያያሪ ባሕሪ የሚያሳየው ሽብርተኝነት በሚያስከትለው ጉዳት የሕዝብ ሠላምና ደህንነት እንዳይናጋ ለማድረግ በቅንጅትና በንቃት እንዲሰሩ አስተዋጽኦ እንዳለው ተነግሯል።

በአዲስ አበባና በመላ አገሪቷ የሚከበሩ ሃይማኖታዊ፣ ባሕላዊና ብሔራዊ ክብረ በዓላት ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበሩ ለማድረግ የፀጥታና የደህንነት ተቋማት አስፈላጊውን ዝግጅቶች በማድረግ ላይ እንደሚገኙ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ኅብረተሰቡ ፀጥታን ሊያውኩ የሚችሉ እንቅስቃሴዎች ሲመለከት በአቅራቢያው ለሚገኙ የፀጥታ አካላት ጥቆማ እንዲሰጥም ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም