የደረቅ ብትን ጭነት የወደብ ኦፕሬሽን መጠናከር በኢትዮጵያና ጅቡቲ መካከል ያለውን የጋራ ተጠቃሚነት ያጎለብታል

79

አዲስ አበባ መስከረም 12/2013 (ኢዜአ) የደረቅ ብትን ጭነት የወደብ ኦፕሬሽን መጠናከር በኢትዮጵያና ጅቡቲ መካከል ያለውን የጋራ ተጠቃሚነት እንደሚያጎለብት የትራንስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ።

በትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ የተመራ የልዑካን ቡድን ከጅቡቲ ፕሬዚዳት እስማኤል ኦማር ጌሌና ከሌሎች የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይቷል።

በኢትዮጵያ አስተማማኝና ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማስመዝገብ ቀልጣፋና ውጤታማ የሎጂስቲክስ አገልግሎት መስጠት እንደሆነ ይታወቃል።

በዚህም ከለውጡ በኋላ የኢትዮጵያን የሎጂስቲክስ አገልግሎት ዘርፍ ለማዘመን ብሄራዊ የሎጂስቲክስ ዘርፍ ፖሊሲና ስትራቴጂ ወጥቷል።

ለፖሊሲው ማስፈጸሚያ ይሆን ዘንድም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ የሎጂስቲክስ ካውንስል ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱ ተገልጿል።

የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግናዊት እንዳሉት፤ ወደ ጅቡቲ ያቀናው የልዑካን ቡድን የደረቅ ብትን ጭነት ላይ የሚያጋጥመውን ችግር በውይይት ለመፍታተ ያለመ ነው።

የሎጂስቲክስ አገልግሎት ዘርፉን ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ ሁለቱ አገራት በትብብር መስራት እንዳለባቸው ሚኒስትሯ ጠቁመዋል።

በዚህም ኢትዮጵያና ጅቡቲ የሕዝቦቻቸውን የጋራ ጥቅም በማስጠበቅ ዘርፉን ለማዘመን የተካሄደው ውይይት ፍሬያማ እንደነበር ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን የወጭና ገቢ ንግድ በከፍተኛ ደረጃ የሚደግፈው የጅቡቲ ወደብ አገልግሎት ጥራትና ፍሰት ከጊዜ ወደ ጊዜ በመሻሻሉ ኢኮኖሚያዊ እድገቱ እየጨመረ መጥቷል ተብሏል።

የኢትዮጵያ የደረቅ ብትን ጭነት በ2012 በጀት ዓመት ከነበረበት አራት ሚሊዮን ቶን በ2013 በጀት ዓመት ወደ አምስት ሚሊዮን ቶን ከፍ ለማድረግ መታቀዱም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም