በኢንቨስትመንት ለመሳተፍ የፈለጉ 22 የሱዳን ባለሃብቶች ያሉበት ቡድን ጎንደር ከተማ ገባ

72

ጎንደር መስከረም 12/2013 (ኢዜአ) የሱዳን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በቱሪዝምና በኢንዱስትሪ ዘርፍ መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ተናገሩ።

22 አባላት ያሉት የሱዳን የባለሀብቶች የልኡካን ቡድን ጎንደር ከተማ ዛሬ ሲደርስ የከተማውና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች አቀባበል አድርገውለታል።

በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ይበልጣል አእምሮ እንደተናገሩት የልኡካን ቡድኑ የመጀመሪያ መዳረሻውን አማራ ክልል በማድረግ የቱሪዝምና የኢንቨስትመንት አማራጮችን ምልከታ ያደርጋል።

በተለይም በገበታ ለሀገር ፕሮግራም የሚከናወኑ ግንባታዎችን ተከትሎ በቱሪዝም ኢንቨስትመንት ላይ ለመሰማራት የሱዳን ባለሀብቶች ፍላጎት እንዳላቸው አምባሳደሩ ተናግረዋል።

የልኡካን ቡድኑ በተጨማሪም በደቡብ፣ በኦሮሚያና በአፋር ክልሎች ተዘዋውሮ ጉብኝት በማድረግ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ለመሰማራት እቅድ አላቸው ብለዋል።

“የልኡካን ቡድኑ በነገው እለት በሰሜን ተራሮችና በጎርጎራ አካባቢ ጉብኝት በማድረግ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ለመሰማራት የሚያስችለውን ምልከታ ያደርጋል” ሲሉም አምባሳደሩ ተናግረዋል።

በልኡካን ቡድኑ አቀባበል ላይ የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሙሉቀን አዳነን ጨምሮ የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሃላፊ ፣የጎንደር ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ተሾመ አግማስና ሌሎች አመራሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም