በአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር የተመራ የልኡካን ቡድን ጎርጎራን አካባቢ እየጎበኙ ነው

64

ባህር ዳር መስከረም 12/2013(ኢዜአ) በአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የተመራ የልኡካን ቡድን የጎርጎራ አካባቢን እየጎበኘ ነው። 

የክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ለኢዜአ እንደገለጹት ጉብኝቱም በሃገር አቀፍ ደረጃ ለተመሰረተው የገበታ ለሃገር ፕሮጀክት አንዱ የሆነውን የጎርጎራ አካባቢ ያለውን ፀጋ አቅም ላላቸው አልሚ ባለሃብቶች ለማሳየት ነው።

ጎርጎራና አካባቢው በርካታ ለቱሪስት መስህብ የሆኑ  የተፈጥሮ ፀጋዎች የታደለ ቢሆንም ከዚህ በፊት ትኩረት ባለመሰጠቱ ሳይለማ መቆየቱን አውስተዋል።

በገበታ ለሃገር ፕሮጀክት የተገኘውን እድል በመጠቀም ንቅናቄ ለመፍጠር ለመጀመሪያ ጊዜ ጉብኝት መደረጉን አመልክተዋል።

በዚህ ጉብኝት 4 ባለሃብቱ ወደ አካባቢው በመሄድ አማራጭ የኢንቨስትመንት ልማቶችን ለማከናወን የመግለፅ፣ የማሳየትና በቀጣይ በልማቱ እንዲሳተፉ ለማነሳሳት እንደሆነ አስረድተዋል።

ለጎርጎራ ፕሮጀክት የክልሉ ካቢኔ፣ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን አመራርና ሌሎችም የወር ደመወዝ ለመስጠት መወሰናቸውን ያመለከቱት አቶ ግዛቸው በቀጣይም ነጋዴውንና ሌላውም ማህበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ እንደሚሰራ አብራርተዋል።

በርዕሰ መስተዳደሩ በተመራው የልኡካን ቡድን የክልሉ አመራሮች፣ ነጋዴዎችና በልማቱ እንደሚሳተፉ  የሚጠበቁ ባለሃብቶችን ያካተተ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም