የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርት ለመጀመር የሚያስችላቸውን ዝግጅት እንዲያደርጉ ተጠየቀ

64

አዲስ አበባ፣ መስከረም 12/2013 (ኢዜአ) የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርት የሚጀመርበት ጊዜ በመንግሥት እስከሚገለጽ ድረስ ትምህርት ለመጀመር የሚያስችላቸውን ዝግጅት እንዲያደርጉ የሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አሳሰበ።

የሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ያዘጋጀውና ትኩረቱን የኮሮና ወረርሽኝን በመከላከል ትምህርት ማስቀጠል ላይ ያደረገ ጉባዔ በጅማ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው።

የሚኒስቴሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች በጉባዔው ታድመዋል።

በውይይቱ ላይ የዩኒቨርሲቲ ተወካዮች እንዳሉት ዩኒቨርሲቲዎች የለይቶ ማቆያና ማከሚያ ማዕከል ሆነው በመቆየታቸው የጥገናና እድሳት ጊዜ የሚጠይቁ በመሆኑ ይህ ሳይድረግ ትምህርት ለመጀመር አስቸጋሪ ነው ብለዋል።

ኮቪድ-19ን በመከላከል ሂደት ሰዎች ራሳቸውን አግልለው እንዲያቆዩ ሌሎች አማራጮች እንዲኖሩም ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሳህረላ አብዱላሂ እንዳሉት በአውሮፓና በአፍሪካ ያሉ አገራት የዓለም ጤና ድርጅት መሥፈርትን ተከትለው ትምህርት ለመክፈት እየተሰናዱ ይገኛሉ።

በኢትዮጵያም መከላከልን መሠረት በማድረግ ከክልልና ዞን ጤና ቢሮዎች ጋር በመሆንና ዩኒቨርሲቲዎችን ከጤናው ዘርፍ ጋር በማስተሳሰር ትምህርት የሚጀመርበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስፍልጋል ብለዋል።

የሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሣሙዔል ኡርቃቶ በበኩላቸው ትምህርት የሚጀመርበት ቀን በመንግሥት እስኪገለጽ ድረስ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዝግጅት እያደረጉ እንዲቆዩ አሳስበዋል።

በዩኒቨርሲቲዎች በኩል ተቋርጦ የቆየውን ትምህርት ለማስቀጠል የተደረገውን ቅድመ ዝግጅት ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ሙሉ ነጋ አብራርተዋል።

በዚህም ትምህርት በተቋረጠበት ጊዜ ተማሪዎች ከትምህርት እንዳይርቁና የሥነ-ልቦና ጉዳት እንዳይደርስባቸው ስለተሠራው ሥራ ጠቅሰዋል።

የድህረ ምረቃ ተማሪዎች በቴክኖሎጂ በመታገዝ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ማድረግ አንዱ መሆኑንም አውስተዋል።

የቅድመ ምረቃ ተማሪዎች በያሉበት የኢንተርኔት አገልግሎት በቅናሽ ዋጋ እንዲያገኙና ከትምህርት እንዳይርቁ ለማድረግ ተሞክሯልም ብለዋል።

የተቋረጠውን ትምህርት በልዩ ሁኔታ ለማጠናቀቅ ኮርስ የጨረሱ የሕግ፣ የሕክምና ቬተርነሪ ተማሪዎችን በአንድ ሣምንት ማካካሻ ለማስጨረስ ታስቧልም ብለዋል።

በሁለተኛ ሴሚስተር ትምህርት ያልጀመሩ ተማሪዎችን በሁለት ወር፣ የሴሚስተሩን 25 በመቶ የተማሩትን ደግሞ በ45 ቀናት ማካካሻ ለማስጨረስም ታስቧል።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ ነባር ተማሪዎችን በሦስት መርሀ ግብር፤ ተመራቂ ተማሪዎችን ደግሞ እስከ ሁለት ወር ለማስጨረስ ታስቧል።

ተመራቂ ያልሆኑ ነባር ተማሪዎች ጉዳይ እየታየ የሚቀጥል ሲሆን ትምህርት ማስቀጠያው ከጥቅምት እንዲጀምርም ታሰቧል።

በአንድ ክፍል ውስጥ ከ25 እስከ 30 ተማሪዎችን ለማስተማር ታቅዷል፤ ሌሎች መማሪያ ክፍሎች ደግሞ የመያዝ አቅማቸውን ግማሽ ብቻ እንዲይዙ ይደረጋል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም