የቤጂንግ የውጭ ጥናቶች ዩኒቨርሲቲ የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት በመጀመሪያ ዲግሪ ደረጃ መስጠት ሊጀምር ነው

75

አዲስ አበባ፣ መስከረም 12(ኢዜአ) የቤጂንግ የውጭ ጥናቶች ዩኒቨርሲቲ የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት በመጀመሪያ ዲግሪ ደረጃ መስጠት ሊጀምር እንደሆነ ተገለጸ።

የዩኒቨርሲቲው የአማርኛ ቋንቋ የመጀመሪያ ዲግሪ መርሃ ግብር ምስረታ ስነ ስርአት ዛሬ በቤጂንግ እየተካሄደ መሆኑን በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ትምህርቱ የሚሰጠው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና የቤጂንግ የውጭ ጥናቶች ዩኒቨርሲቲ ባደረጉት የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት አማካኝነት ነው።

በስምምነቱ የቤጂንግ የውጭ ጥናቶች ዩኒቨርሲቲ የአማርኛ ቋንቋ ትምህርትን በመጀመሪያ ዲግሪ ደረጃ ይሰጣል።

በዚሁ መሰረት የአማርኛ ቋንቋ በቻይና የትምህርት ተቋም ለመጀመሪያ ጊዜ ይሰጣል።

የምስረታ መርሃ ግብሩ ላይ የቤጂንግ የውጭ ጥናቶች ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ጂያ ውንጂንና በቻይና የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተወካይ አቶ ሳሙኤል ፍጹምብርሃን ተገኝተዋል።

የቤጂንግ የውጭ ጥናቶች ዩኒቨርሲቲ እ.አ.አ በ1941 የተመሰረተ ሲሆን በቻይና በውጭ ቋንቋዎች ጥናት ላይ ትኩረት አድርጎ የተቋቋመ የመጀመሪያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ነው።

ዩኒቨርሲቲው በቅድመ ምረቃና በድህረ ምረቃ የውጭ አገራት ዜጎችን ጨምሮ በአሁኑ ወቅት ከ8 ሺህ 500 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ ይገኛል።

ለመማር ማስተማር ሥራውም ከ2 ሺህ 400 በላይ የአካዳሚ ሠራተኞች እንዳሉት ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም