ሃገራቱ በግድቡ ድርድር ዙሪያ የጋራ ተጠቃሚነት መሰረት በማድረግ መስማማት ይችላሉ - የኢጋድ ስራ አስፈፃሚ

97

አዲስ አበባ፣ መስከረም 12/2013 (ኢዜአ) በታላቁ የህዳሴ ግድብ ድርድር ላይ ግብፅ እና ኢትዮጵያ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ መግባባትና ከስምምነት መድረስ አለባቸው ሲሉ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ዋና ጸሃፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ገለጹ።

ዋና ጸሀፊው ከሩሲያው ስፑትኒክ ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ እንደገለጹት ኢጋድ የኢትዮጵያንም ሆነ የሱዳነና የግብጽን ስጋት ግምት ውስጥ ባስገባ መንገድ በድርድር መፍትሄ እንደሚመጣ ያምናል፡፡

ኢትዮጵያና ግብጽ እኩል አሸናፊ የሚያደርጋቸውን መፍትሄ ማግኘት የሚችሉት በውይይት መሆኑን ያነሱት የወቅቱ የኢጋድ ዋና ጸሃፊና እኤአ ከ2016 እስከ 2019 የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉት ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ አንዳቸው ለሌላው ሰላምና ትብብርን ካስቀደሙ ውዝግቡ በቀላሉ የሚፈታ ስለመሆኑም አንስተዋል።

ለውዝግቡ መፍትሄ ለመስጠት ከኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ በተውጣጡ ሚኒስትሮች እየተካሄደ ነበረው መቋረጥ እንደሌለበትም ዋና ጸሃፊው ስለመግለጻቸው በዘገባው ተጠቅሷል።

የግድቡ ተግባራዊ መደረግ የውሃ ደህንነታችንን ይነካል የሚል ስጋት ግብጽና ሱዳን ተቃውሞዋቸውን ቢያሰሙም እውነታው ግን የጋራ ተጠቃሚነትን ያስቀደመ ስለመሆኑ የዘርፉ ምሁራን ያስረዳሉ።

ኢትዮያ በአባይ ውሃ ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን በማስቀደም በአፍሪካ ትልቁ የሆነውን የውሃ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ እየገነባች መሆኑን ዘገባው አስታውሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም