የዓለማችን ሁለት ሦስተኛ አገሮች የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ክትባትን ተደራሽ ለማድረግ ያለመውን ጥምረት ተቀላቀሉ

57

አዲስ አበባ፣ መስከረም 12/2013 (ኢዜአ) የዓለማችን ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑ አገሮች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ክትባትን ተደራሽ ማድረግን ዓላማ ያደረገውን ጥምረት መቀላቀላቸውን የዓለም የጤና ድርጅት አስታወቀ።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተውን ወረርሽኝ ለመግታት ለሁሉም አገሮች ፈጣን፣ ፍትሐዊና እኩል የኮቪድ-19 ክትባት ተደራሽነትን ዓላማ ያለው ጥምረት (ኮቫክስ) በሐምሌ ወር 2012 ዓ.ም መመሥረቱ የሚታወስ ነው።

በጥምረቱ አማካኝነት የበለጸጉ አገሮች ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ካላቸው አገሮች ጋር በመተባበር በቢልና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን አማካኝነት በተቋቋመው በጋቪ የክትባት ጥምረት በተዘጋጀ ፕሮጀክት የክትባት ተደራሽነት ለማስፋት የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋሉ።

የዓለም የጤና ድርጅት 46 ከፍተኛ የኢኮኖሚ ገቢ ያላቸው አገሮች ኮቫክስን መቀላቀላቸውን አስታውቋል።

አውስትራሊያ፣ ካናዳ፣ ጃፓን፣ ፈረንሣይ፣ ጀርመን፣ ኢራን፣ እሥራኤል፣ ሜክሲኮ፣ ኩባ፣ ኦስትሪያ፣ ቤልጂየም፣ ሲንጋፖር ጥምረቱን ከተቀላቀሉ አገሮች መካከል ይገኙበታል።

ደቡብ አፍሪካ፣ ቦትስዋና፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ጋቦንና ናሚቢያ ከአፍሪካ ጥምረቱን የተቀላቀሉ ናቸው።

ይህም በዓለማችን ላይ ጥምረቱን የተቀላቀሉትን አገሮች ቁጥር ወደ 156 ማድረሱንና ከዓለም አገራት ሁለት ሦስተኛ ገደማ የሚሆኑትን የሚሸፍን እንደሆነ ገልጿል።

በቀጣይ ቀናትም 38 አገሮች የክትባት ጥምረቱን ይቀላቀላሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የዓለም የጤና ድርጅት አመልክቷል።

የጋቪ የክትባት ጥምረት ዓለም አቀፍ ተቋም ከዓለም አቀፍ ክትባት አምራቾችና አበልጻጊዎች ጋር ሥምምነቶችን መፈራረም ይጀምራል ተብሏል።

በሥምምነቶቹ አማካኝነት በኮቫክስ ጥምረት ውስጥ የሚገኙ አገሮች እስከ 2021 መጨረሻ ለወረርሽኙ ክትባቶችን ማግኘት ያስችላቸዋል።

በጋቪ የክትባት ጥምረት ኢትዮጵያን ጨምሮ ዝቅተኛና ዝቅተኛ መካከለኛ ኢኮኖሚ ያላቸው ተብለው የተለዩ 92 አገሮች በጥምረቱ አማካኝነት የክትባቶች ተጠቃሚ ይሆናሉ።

ጥምረቱ የፋይናንስና ሣይንሳዊ ሀብቶችን በማጣመር ክትባትን ፍትሐዊ በሆነ መልኩ ተደራሽ ለማድረግ ያለው አስተዋጽኦ ወሳኝ መሆኑ ተገልጿል።  

ኮቫክስ አሁን ቢዝነስ ሆኗል የተለያዩ አገሮች ለራሳቸው ሕዝብ ክትባት ለማግኘት ብቻ ሳይሆን ክትባቶች ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ አገሮች ተደራሽ እንዲሆን በትብብር እየሠሩ መሆናቸውን የጋቪ የክትባት ጥምረት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ሴዝ ቤርክሌይ ተናግረዋል።

በጋቪ የክትባት ጥምረት ከለጋሽ አገሮች፣ ከግሉ ዘርፍና ከበጎ አድራጊዎች 700 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል።

እስከ 2020 መጨረሻ ለክትባት ተደራሽነት ለመነሻ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ እንደሚያስፈልግ ተነግሯል።

በገንዘብ ድጋፉ ሁለት ቢሊዮን የክትባት መጠኖች በማምረት አንድ ቢሊዮን ሕዝብ የክትባት ተጠቃሚ ለማድረግ ዕቅድ መያዙም ተጠቅሷል።

ሁሉም አገሮች የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ክትባት ተደራሽ ማድረግን ዓላማ ያደረግውን ጥምረት እንዲቀላቀሉ የዓለም የጤና ድርጅት ጥሪውን አቅርቧል።

አሜሪካ የኮቪድ-19 ክትባትን ለማግኘት ዓለም አቀፍ ጥምረቱን እንደማትቀላቀል በፕሬዚዳንቷ ዶናልድ ትራምፕ በኩል ገልጻለች።

ጥምረቱን የማትቀላቀለው የዓለም ጤና ድርጅት የጥምረቱ አካል በመሆኑ እንደሆነም ተናግረዋል።

በሐምሌ ወር 2012 ዓ.ም መጀመሪያ አሜሪካ ከዓለም ጤና ድርጅት ለመውጣት የወሰነች ሲሆን ለዚህም ምክንያት ያለችው ድርጅቱ በቻይና ተፅዕኖ ሥር የሚገኝ በመሆኑ እንደሆነ ገልጻለች።

ጋቪ የክትባት ጥምረት ዓለም አቀፍ ተቋም በዓለም ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ የሚገኙ አገሮች የሕፃናት ክትባቶችን ተደራሽንት ማሻሻል ላይ የሚሠራ ነው።

እስካሁን ድረስ በዓለም ዙሪያ በሙሉ ጥቅም ላይ እንዲውል የተፈቀደ የኮሮና ቫይረስ ክትባት የለም።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም