ዞኖቹ 6ሺህ 763 ቶን የታጠበ ቡና ለገበያ አቀረቡ

134

ነቀምቴ መስከረም 11/2012 (ኢዜአ) ከምዕራብና ቄለም ወለጋ ዞኖች በተጠናቀቀው በጀት አመት 6ሺህ 763 ቶን የታጠበ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለሥልጣን አስታወቀ።

የባለስለጣኑ  የግምቢ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ለማ በፍቃዱ ለኢዜአ እንደገለጹት በበጀት አመቱ ለገበያ የቀረበው የቡና መጠን ካለፈው አመት በ900 ቶን ብልጫ አለው።

ለገበያ ከቀረበው ቡና ውስጥ 65 በመቶው ከምዕራብ ወለጋና 34  በመቶው ከቄለም ወለጋ መሆኑን ተናግረዋል ።

ቀሪው አንድ በመቶ የሚሆነው ቡና በህገ-ወጥ ዝውውር ተይዞ ለገበያ የቀረበ መሆኑን ጠቅሰዋል ።

በበጀት አመቱ ከዞኖቹ ለማዕከላዊ ገበያ የቀረበው ቡና ካለፈው አራት አመት ወዲህ ከቀረበው በመጠን ከፍተኛ መሆኑንም ተናግረዋል ።

በቅርንጣፍ ጽህፈት ቤቱ በኩል የቀረበው የቡና መጠንም እንደ ሀገር አንደኛ ደረጃን መያዙን ስራ አስኪያጁ ገአስታውቀዋል ።

በጀት ዓመቱ ከዞኖቹ ለማዕከላዊ ገበያ ከቀረበው ቡና  21 ሚሊዮን 331 ሺህ 240 ዶላር ገቢ መገኘቱን የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የገበያ መረጃ ትንተና ቡድን መሪ አቶ ትዕዛዙ ኢዶሣ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም