ዘላቂ የመሬት አጠቃቀም ስርአት ለአካባቢ ጥበቃና ለምርት መጨመር አስተዋጻ አድርጓል

62

ሀዋሳ መስከረም 11/2013 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል ተግባራዊ የሆነው ዘላቂ የመሬት አጠቃቀም ስርአት ለአካባቢ ጥበቃና ምርታማነት እደገት አስተዋጾ እያደረገ መሆኑን የክልሉ የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ኤጀንሲ አስታወቀ።

በኤጀንሲው የመሬት አጠቃቀም ዕቅድ ዝግጅት ቡድን መሪ አቶ ብዙአየሁ ሰለሞን ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ የተዘረጋው ዘላቂ የመሬት አጠቃቀም ስርአት በተመረጡ 470 ቀበሌዎች በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ ሲደረግ ቆይቷል።


ከዚሁ ጎን ለጎን የመሬት አጠቃቀም አዋጅና ደንብ ወጥቶ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።

በቀበሌዎቹ ከ376 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ባለው አቀማመጥ፣ በውሀ ይዞታው፣ በአፈሩ ሁኔታ፣ በአየር ንብረት፣ በዝናብ መጠንና መሰል መስፈርቶች መሰረት ያደረገ ፕላን በማዘጋጀት ወደ ተግባር መገባቱን አስታውቀዋል። 

መሬቱን በስምንት ደረጃ በመከፋፈልና የእርሻና የደን ይዞታዎችን በመለየት ለልማት እንዲውል በመደረጉ በአካባቢ ጥበቃና በሰብል ምርታማነት ላይ አዎንታዊ ለውጥ መምጣቱን አመላክተዋል ።


ከዚህ ቀደም ባህር ዛፍ ተክለው ያለሙ የነበሩ አርሶ አደሮችም ማሳቸውን ወደ ሰብል ልማት በመቀየራቀቸው ውጤታማ መሆናቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል ።

ያለአግባብ ለእርሻ ስራ የዋሉ ተዳፋት መሬቶችም ተከልለው ለደን ይዞታ እንዲውሉ በመደረጉ ተመልሰው ያገገሙበት ሁኔታ መፈጠሩን ጠቅሰዋል ።


በሀድያ ዞን ጊቤ ወረዳ ዋሬ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር በቀለ ኤርዶ በበኩላቸው በእርሻ ማሳቸው ላይ የተከሉትን ባህርዛፍ በማንሳት ሙሉ ለሙሉ ለሰብል ልማት በዋላቸው የተሻለ ምርት ማግኘት መቻላቸውን ተናግረዋል ።


ከባለሙያ የተሰጣቸውን ምክረ ሀሳብ በግብአትነት መጠቀማቸውም ውጤታማ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል። 


አሁን ላይ ስንዴና ገብስ እንዲሁም ሙዝ፣ ቡናና የመኖ ሳር በማልማት ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉ አብራርተዋል።

“በተዳፋት መሬት ላይ ከማለማው ሰብል አገኘው የነበረው ምርት እጅግ አነስተኛ ነበር” ያሉት ደግሞ በጎፋ ዞን ኦይዳ ወረዳ ኡባዳማ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ግማዶ ክባሴ ናቸው።


ማሳቸው ላይ የአፈርና ወሀ ጥበቃ ስራ በመስራታቸውና መልሶ በማገገሙ ምርታማነቱ መጨመሩን ጠቁመው አሁን ላይ እያለሙ ካለው ቦሎቄና በቆሎ እንዲሁም ሙዝ የተሻለ ምርት እያገኙ መሆኑን ገልጸዋል ።


በወረዳው ኡባደማ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ዱሬታ ኑሬ በበኩላቸው የእርሻ ማሳቸው ተራራማና ተዳፋማ በመሆኑ አፈሩ በጎርፍ እየታጠበ ስለሚሄድ የሚያገኙት ምርት አነስተኛ እንደነበር አስታውሰዋል።


ከሌሎች 57 አርሶ አደሮች ጋር በመሆን ማሳቸውን በመልቀቅ ለደን ልማት ተከልሎ እንዲያገግም መደረጉን ጠቅሰዋል ።


በተሰጣቸው ተለዋጭ መሬት ላይ በጀመሩት የሰብል ልማት ምርታማነታቸውን ማሳደግ እንደቻሉ ተናግረዋል ።

በኦይዳ ወረዳ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት የዘላቂ መሬት አጠቃቀም ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ጸደቀ ኤልያስ በወረዳው በህዝብ ቁጥር መጨመርና በእርሻ መሬት መስፋፋት ምክንያት የተጎዳ 350 ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ያለአግባብ ለእርሻ የዋለ 200 ሄክታር መሬት አርሶ አደሮች ተነስተው በመከለሉ መልሶ ማገገሙን ለአብነት ጠቅሰዋል ።

ከማሳቸው የተነሱና ተለዋጭ መሬት የተሰጣቸው አርሶ አደሮች በከብት ማድለብ፣ በንብ ማነብ፣ በእንስሳት በመኖ በሙዝና ሰብል ልማት ተሰማርተው ውጤታማ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም