የአዋሽ ወንዝ ጎርፍ ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ንብረት በአፋር ክልል አወደመ - የክልሉ መንግስት

111

አዲስ አበባ፣ መስከረም 11/2013 ( ኢዜአ) በአፋር ክልል የአዋሽ ወንዝ ባስከተለው የጎርፍ አደጋ ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙን የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ቢሮ ገለጸ።

ለጎርፍ ተፈናቃዮች የሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስና በዘላቂነት ለማቋቋም 350 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግም ቢሮው አስታውቋል።

የአፋር ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ቢሮ ኃላፊ አቶ መሀመድ ሁሴን ለኢዜአ እንዳሉት፤ የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ ባስከተለው ጎርፍ 240 ሺህ ዜጎች ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ከክረምቱ ዝናብ መጨመርና በአዋሽ ወንዝ ላይ የተገነቡት የከሰም፣ ተንዳሆና ቆቃ ግድቦች ውሃ ሞልቶ በመፍሰሱና አካባቢው በጎርፍ በመጥለቅለቁ ከ144 ሺህ በላይ ዜጎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል ብለዋል።

የአዋሽ ወንዝ ሙላት ያስከተለው ጎርፍ በ41 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የደረሰ ሰብልና በዘር ለመሸፈን በተዘጋጀ 18 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ጉዳት አድርሷል ብለዋል።

በክልሉ 105 ትምህርት ቤቶች፣ 200 የገጠር መንገዶችና 6 ድልድዮችም በጎርፍ ምክንያት ፈርሰዋል።

ጎርፉ ከ21 ሺህ በላይ የቤት እንስሳትን መውሰዱም ተገልጿል።

በውሃ የተከበቡ ተፈናቃዮችን ለማውጣትና ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ የክልሉና የፌደራል መንግስት እንዲሁም የተለያዩ ድርጅቶችና ተቋማት ጥረት እያደረጉ ቢሆንም አሁንም በቂ አይደለም ነው ያሉት አቶ መሀመድ።

የአፋር ክልል በበረሃ አንበጣና በኮቪድ-19 እየተፈተነ መሆኑን ገልጸው፤ በጎርፍ ለተፈናቀሉት የሚቀርብ አስቸኳይ የመድሃኒት፣ የንጹህ መጠጥ ውሃና መጠለያ እጥረት እንዳለም ገልጸዋል።

በጎርፍ ለተፈናቀሉ ዜጎች ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስና በዘላቂነት ለማቋቋም 350 ሚሊዮን ብር የሚያስፈልግ ቢሆንም እስካሁን የተሰበሰበው 100 ሚሊዮን ብር ብቻ መሆኑንም ተናግረዋል።

በመሆኑም ችግሩ እልባት እንዲያገኝ መንግስትና የተለያዩ ተቋማት የሚያደርጉት ድጋፍ ቀጣይነት እንዲኖረው ጠይቀዋል።

በኢትዮጵያ ካለፈው ሚያዚያ ወር ጀምሮ እስካሁንም በተለያዩ አካባቢዎች እየጣለ ያለው ከባድ ዝናብ ጎርፍ በማስከተሉ ጉዳቶች እየደረሱ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም