ትምህርት ቤቶች ትምህርት ከመጀመራቸው በፊት የቅድመ ጥንቃቄና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በቅድሚያ መሠራት አለበት

60

አዲስ አበባ፣ መስከረም 10/2013(ኢዜአ) ትምህርት ቤቶች ትምህርት ከመጀመራቸው በፊት የቅድመ ጥንቃቄና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በቅድሚያ መሠራት እንዳለባቸው ተጠቆመ።

በጤና ሚኒስቴር በኩል በቀረበው የኮቪድ -19 ምክረ ሀሳቦች ላይ ቋሚ ኮሚቴዎች ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሄዷል።

የሴቶች፣ ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳዮችና የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች በጤና ሚኒስቴር በኩል በቀረበው የኮቪድ- 19 ምክረ ሀሳቦች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ውይይት ካደረገባቸው ጉዳዮች ውስጥ በቀጣይ ትምህርትን እንዴት ማስጀመር እንደሚቻል መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል።

በተለይ ለአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ቅድሚያ ተሰጥቶ ለመጀመር መታቀዱ እንዳለ ሆኖ በዩኒቨርስቲዎችና ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ማዕከሎችም ላይ ትምህርትን ለማስጀመር ምን ምቹ ሁኔታ አለ በሚለው ላይ ከቋሚ ኮሚቴዎቹ በስፋት ጥያቄ መነሳቱ ተገልጿል።

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ ትምህርት ቤቶች በኮቪድ- 19 ምክንያት በ2012 ዓ.ም አጋማሽ ለመቋረጥ መገደዳቸውና ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው ተቋማት ውስጥ ዋነኞቹ መሆናቸውን ለቋሚ ኮሚቴው ገልጸዋል።

አቶ ሚሊዮን አያይዘውም ከ26 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ተፈናቅለው ወደ የቤታቸው እንደተመለሱ አስረድተዋል።

በዚህም የተነሳ በሕፃናት አዕምሯዊ ዕድገት፣ በትምህርት ፍላጎታቸው ላይ እና ያለዕድሜ ጋብቻ በአጠቃላይ ማኅበራዊ ቀውሶችን እያስከተለባቸው እንደሚገኝ አንስተዋል።

አክለውም እንደ ዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ከሆነ ኮቪድ 19 ከሰዎች ጋር የሚቆይ በሽታ በመሆኑ ትምህርትን ለማስጀመር የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት ላይ መሆኑን አቶ ሚሊዮን አመልክተዋል፡፡

የመማር ማስተማሩን ሂደት ጤናማ ለማድረግ በወጣው መመሪያ አዲስ ስታንዳርድ ወጥቶ ከዚህ በፊት እስከ 60 ተማሪዎችን የሚይዘው የመማሪያ ክፍል ከ20 እስከ 25 ተማሪዎችን ብቻ እንዲይዝ መደረጉንም አስረድተዋል።

አቶ ሚሊዮን አያይዘውም በዋናነትም አስፈላጊውን የበሽታ መከላከያ ቁሳቁስ ለማሟላት አቅራቢ ድርጅቶች ጋር በመነጋገር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የክፍል ተማሪ ጥምርታን በማሻሻል ተጨማሪ ማስፋፊያ ያደረጉ ክልሎች እንዳሉና መጀመሪያም የነበረው ጥምርታ ዝቅተኛ በሆነባቸው አካባቢዎችና ክልሎች ላይ አሁንም ባለው ሁኔታ ትምህርን ማስቀጠል የሚቻልበት ሁኔታ መኖሩንም ገልጸዋል፡፡

የ8ኛ ክፍልና የ12ኛ ክፍል ፈተናዎችን ለመስጠት በዝግጅት ላይ መሆኑንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሣሙዔል ክፍሌ በበኩላቸው በመጀመሪያ ድግሪ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ለማስቀጠል በርካታ የትምህርት ቁሳቁስ ባለመኖሩ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የተቋረጠ መሆኑን ገልጸዋል።

ሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች የገጽ ለገጽ ትምህርት ባለማስፈለጉ በተለያዩ ዘዴዎች ትምህርቱ ሲሰጥ መቆየቱንና አብዛኛዎችም እየተመረቁ መሆናቸውን አንስተው በቀጣይ ለተመራቂ ተማሪዎች ቅድሚያ እንደሚሰጥም አመልክተዋል።

ይሁን እንጂ ምዝገባ ቢጀመርም ትምህርት የሚጀመርበት ቀንና ሁኔታ አሁን ላይ እንደማይታወቅ ገልጸዋል።

በቀጣይ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በጋራ በመሆን ጤናማ የትምህርት አጀማመር ዝግጅቱ ሲጠናቀቅና በትክክለኛው ቁመና ላይ ሲደረስ የሚታወቅ መሆኑን ዶክተር ሣሙኤል ተናግረዋል።

የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሰሀርላ አብዱላሂ በበኩላቸው የኮቪድ 19 በሽታ በዚህ ጊዜ ይቆማል የሚል ሣይንሳዊ የሆነ መረጃ እንደሌለ ገልጸዋል።

አገሪቱ ዩኒቨርስቲዎችን ለለይቶ ማቆያነት ስትጠቀምባቸው ስለነበር እነዚህን የትምህርት ተቋማት የማጽዳት ሥራም መሥራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ዩኒቨርስቲዎች ራሳቸው ሳኒታይዘርና ማስክ የመሳሰሉ የጤና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን እያመረቱ ስለሆነ የጤና መጠበቂያ ቁሳቁሶች እጥረት የሚቀረፍና ለጤናማ የትምህርት ዝግጁነት እንደሚረዳም ተናግረዋል።

ቋሚ ኮሚቴዎቹ በሰጡት ማጠቃለያ የተጀመረው የተማሪዎች ምዝገባ ቢጀመርም የትምህርት አጀማመሩን በተመለከተ በኅብረተሰቡ ዘንድ የግንዛቤ ክፍተት እንዳለ አንስተዋል።

ቋሚ ኮሚቴው አያይዞም ትምህርት እስኪጀመር ባሉት ጊዜያት ሚኒስቴሩ ከባለድርሻና ከኅብረተሰቡ ጋር ግንዛቤን የማስጨበጥ ሥራ መሥራት እንዳለበት ማሳሰባቸውን ምክር ቤቱ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም