በደቡብ ክልል የአርብቶ አደሩንና የባለሀብቱን የልማት ተሳትፎ ለማጠናከር ትኩረት ተሰጥቷል - አቶ ርስቱ ይርዳው

59

ሐዋሳ፣ መስከረም 10/2013 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ የአርብቶ አደሩንና የግል ባለሀብቱን ተሳትፎ ለማጠናከርና ለማበረታታት መንግሥት እንደሚሠራ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው አስታወቁ።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በደቡብ ኦሞ ዞን ኛንጋቶም ወረዳ በባለሀብቶች የለማ የእርሻ እንቅስቃሴን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

በዚህ ወቅት አቶ ርስቱ እንዳሉት ለክልሉ ዕድገትና ልማት መረጋገጥ የሁሉንም አካል ተሳትፎ ስለሚጠይቅ መንግሥት የግል ባለሀብቱንና የአርብቶ አደሩን ማኅበረሰብ የልማት ተሳትፎ ለማጠናከር ይሰራል።

በተለይ በኦሞ ወንዝ ሙላት ሳቢያ ለተፈናቀሉ አርብቶ አደሮች የቤት እንስሳት የመኖ እጥረት ለመቅረፍ በባለሀብቱ ተሳትፎ የመኖ ልማት መጀመሩን አድንቀዋል።

“በአርብቶ አደሩ አካባቢ እየተካሄደ ባለው የመስኖ ልማት ሥራ የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማሳደግ ይቻላል” ያሉት አቶ ርስቱ በቀጣይም በዘርፉ የሚካሄደውን ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ ለማጎልበት በትኩረት እንደሚሠራ አስታውቀዋል።

የደቡብ ክልል አርብቶ አደርና ልዩ ድጋፍ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ አቶ ምትኩ ታምሩ በበኩላቸው የወንዙ ሙላት ባስከተለው ጎርፍ አደጋ ከአካባቢያቸው የተፈናቀሉ የአርብቶ አደሮችንና የቤት እንስሳትን ሕይወት ለመታደግ ለመኖ አቅርቦት ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።

በአርብቶ አደሩ ማኅበረሰብ እየለማ ያለው የእንስሳት መኖ በቂ ባለመሆኑ የግል ባለሀብቱን በማሳተፍ ዘርፉን ለማሻሻል እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

አርብቶ አደሩን ውኃን መሠረት ያደረገ በመንደር የማሰባሰብ ሥራ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ሲከናወን መቆየቱን የገለጹት ኃላፊው ባለፉት ዓመታት የአርብቶ አደሩን የልማት ፍላጎቱን ለማሟላት የተደረገው ጥረት በሚፈለገው ልክ ውጤታማ እንዳልሆነ ጠቁመዋል።

በቀጣይ በዘርፉ የተስተዋሉ ውስንነቶችን ለመቅረፍ ቢሮው ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሠራ መሆኑን ገልጸው የአሁኑ ጉብኝትም ይሄንኑ ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ አመላክተዋል።

በወረዳው ከሚገኙ የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬ አምራች ባለሀብቶች መካከል አቶ ሲሣይ ተስፋዬ እንዳሉት በ120 ሄክታር መሬት ላይ ፓፓዬ በመስኖ በማልማት በየቀኑ ከፍተኛ ምርት ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ ሆነዋል።

ከኦሞ ወንዝ ሙላት ጋር ተያይዞ አርብቶ አደሩ ለቤት እንስሳት ያጋጠመውን የግጦሽ እጥረት ለመቅረፍም የመኖ ልማት በስፋት እያካሄዱ መሆኑን ገልጸዋል።

በአካባቢው ያለውን ለም አፈርና ውኃ በማቀናጀት ማልማት ከተቻለ በአጭር ጊዜ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻልም እምነታቸውን ገልጸዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የሚመራው ልዑክ ዛሬ ወደ ዳሰነች ወረዳ በማቅናት በኦሞ ወንዝ ሙላት ሳቢያ የተፈናቀሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም