የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ 8ሺ 152 ተማሪዎችን አስመረቀ

65
ሐረር ሐምሌ 7/2010 የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ከመማር ማስተማሩ በተጓዳኝ የሀገሪቱን የእድገት ጉዞ በመከተል በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት ውጤታማ ስራዎች እያከናወነ መሆኑን ገለጸ፡፡ ዩኒቨርሲቲ በተለያየ የትምህርት መስክ ያሰለጠናቸውን 8ሺ 152 ተማሪዎችን ዛሬ አስመርቋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ተወካይ ዶክተር ጀማል ዩስፍ በምረቃው ስነስርዓት ወቅት እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው ችግር ፈቺ ምርምር በማካሄድ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ሲሰራ ቆይቷል። በ2010 ዓ.ም እያካሄዳቸው ካሉት 358 አዲስና ነባር የምርምር ፕሮጀክቶች ውስጥ የ44ቱ ስራ መጠናቀቁን ገልጸዋል። በማህበረሰብ አገልግሎትም ዩኒቨርስቲው ለአካባቢው ጤና ተቋማት የህክምና መገልገያ ቁሳቁሶች፣ መድኃኒቶች፣ ለወጣቶች የገበያ ማዕከል በመገንባት፣ ከ100 ሺህ በላይ አቅመ ደካማ ለሆኑ ዜጎች ነጻ የህግ አገልግሎት ሰጥቷል። ለትምህርት ቤቶች የማጣቀሻ መጽሐፍት፣ ለ315 አካል ገዳተኞች ነጻ የሰው ሰራሽ አካል እንዲሁም ለአካባቢው ማህበረሰብ መንገድ፣ የንጹህ መጠጥ ውሃና ሌሎች የልማት ስራዎች አከናውኗል። በመማር ማስተማሩም መስክ ዩኒቨርስቲው በአሁኑ ወቅት የመጀመሪያ ዲግሪን ወደ 74፣ ሁለተኛ ዲግሪን ወደ 93 እና የዶክትሬት ዲግሪን ደግሞ ወደ 27 ዘርፎች አሳድጓል። ተቋሙ ዘንድሮ ካስመረቃቸው ተማሪዎች መካከል 43 በዶክትሬት ዲግሪ፣ 810 በሁለተኛ ዲግሪና ቀሪዎቹ ደግሞ በመጀመሪያ ዲግሪ ፕሮግራሞች ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ መሆናቸውን ዶክተር ጀማል ተናግረዋል፡፡ ከነዚህም መካከል 24 ነጥብ 6 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው። ተመራቂዎቹ በመደበኛ፣ በተከታታይ፣ በርቀትና በክረምት መርሃ ግብር ከሰለጠኑባቸው መስኮች መካከል ግብርና፣ አካባቢ ሳይንስ፣ አግሮ ኢንዱስትሪና መሬት ሃብት፣ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ፣ ህክምናና ማህበረሰብ ሳይንስ ይገኙበታል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የየእለቱ ክብር እንግዳ ወይዘሮ ጠይባ ሐሰን  ወጣት ምሁራን ስራ ፈጣሪና ታታሪ በመሆን ራሳቸውን፣ ቤተሰቦቻቸውንና ሀገራቸውን ማገዝ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ መንግስትና ህዝብ የጣለባቸውን ኃላፊነትን ህብረተሰቡን በቅንነትና በታማኝነት በማገልገል ለሌሎች ወጣቶች አርአያ መሆን እንደሚጠበቅባቸውም ጠቁመዋል፡፡ "ተመራቂ ተማሪዎቹ የበለጸገችና ዴሞክራሲ የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመገንባት የተጀመረውን ጥረት ማጠናከር ይኖርባቸዋል" ብለዋል። በዕለቱም ዩኒቨርሲቲው ለአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ለአቶ ገዱ አንዳርጋቸው የስራ አመራርና የማህበረሰብ ለውጥ በማምጣት እንዲሁም በቅጽል ስሙ መሀመድ ቆፔ ለሚጠራው ጋዜጠኛና አርቲስት መሐመድ አህመድ በስነጽሑፍና በኪነ ጥበብ  ላበረከቱት አስተዋጽኦ የክብር ዶክትሬት ተሰጥቷቸዋል። ከተመራቂዎች መካከል በህግ ትምህርት 3 ነጥብ 85 በማምጣት በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቀችው ማህሌት አብራሃም በሰጠችው አስተያየት በሰለጠነችበት ሙያ ሀገሯንና ያስተማራትን  ህዝብ ለማገልገል ጠንክራ እንደምትሰራ ተናግራለች፡፡ በሰነ ህይወት ትምህርት የማዕረግ ተመራቂ ነጂብ  ሼህ አብዱልዋሂድ "ስራ ፈጥሬ በመንቀሳቀስ ያለኝን ክህሎት ለወጣቶች ለማካፈል ዝግጁ ነኝ" ብሏል፡፡ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ከተመሰረተ ጀምሮ ከ80 ሺህ በላይ ምሁራንን ከዲፕሎማ እስከ ዶክትሬት ዲግሪ የትምህርት ደረጃ አሰልጥኖ ማስመረቁም ተመልክቷል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም