ንጹህ አካባቢን ለመፍጠር የአካባቢ ጽዳትን ባህል ማድረግ ይገባል

123

ባህርዳር፣ መስከረም 9/2013( ኢዜአ) ህብረተሰቡ እይታን የሚስብ ከተማና አካባቢን ከመፍጠር ባለፈ ጤንነቱን በዘላቂነት ለመጠበቅ የፅዳት ባህሉን ሊያሳድግ ይገባል ሲሉ የአማራ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ ተናገሩ።

የብልፅግና ፓርቲ ሰልጣኞች በባህርዳርና ደሴ ከተሞች የፅዳት ዘመቻ አካሄደዋል።

''ባህር ዳርን እወዳለሁ፤ ፅዳቷንም እጠብቃለሁ'' በሚል መሪ ቃል የዓለም የፅዳት ቀንን ምክንያት በማድረግ በተካሄደው የፅዳት ዘመቻ የተገኙት ዶክተር ሰይድ ኑሩ እንዳሉት የሰው ልጅ ትልቁ ሃብቱ ጤናው ነው።

ጤናውን ለመጠበቅ ደግሞ ቁልፉና የበሽታ መከላከያው መንገድ ዘወትር የግልና የአካባቢን ንጽህናን መጠበቅ፣ ቆሻሻን አፅድቶ ለጤና ጠንቅ በማይሆን ቦታ አርቆ ማስወገድ እንደሚገባ ተናግረዋል። 

የጽዳት ዘመቻውም የባህር ዳር ከተማን ፅዱ፣ ሳቢ፣ ማራኪና አረንጓዴ ገጽታዋን በመጠበቅ ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ ከተማ ለማድረግ እንደሆነ ገልፀዋል።

“አካባቢያችንን ከቆሻሻ ማፅዳት ከተማዋ የጎብኝዎቿን ቀልብ እንድትስብ ያደርጋል” ያሉት ደግሞ በፅዳት ዘመቻው የተሳተፉትና የብልፅግና ፓርቲ የ2ኛ ዙር ሰልጣኝ አቶ ጌታቸው ቢያዝን ናቸው። 

“ዘወትር አካባቢያችንንና ከተማችንን ካፀዳን ሊከሰቱ ከሚችሉ ተላላፊ በሽታዎች እንድንጠብቅ ያስችለናል” ብለዋል።

ከደቡብ ጎንደር ዞን ላይ ጋይንት ወረዳ የመጡትና በፅዳት ዘመቻው የተሳተፉት ሌላኛው ሰልጣኝ አመራር አቶ ጌታሰው አምሳሉ በበኩላቸው እንዳሉት በፅዳት ዘመቻው ስንሳተፍ ህብረተሰቡ የአመራሩን ቁርጠኝነት በተግባር እንዲያይ ያስችለዋል።

በተመሳሳይ የደቡብ ወሎና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞንና ደሴ ከተማ አስተዳደር የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ከህብረተሰቡ ጋር በደሴ ከተማ የፅዳት ስራ ተከናውኗል።

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መልካሙ አብጤ እንደገለጹት በከተሞች የሚስተዋለውን ቆሻሻ በዘላቂነት በማስወገድ ለጤና መታወክ ምከንያት የማይሆን አካባቢ ለመፍጠር በቅንጅት መስራት ይገባል።

ከኮሮና ቫይረስ ራስን ለመጠበቅም ንጽህናን መጠበቅ ያስፈልጋል ያሉት ኃላፊው ፤ በመጥፎ ሽታ ከሚመጣ የመተንፈሻ አካባቢ በሽታዎችም ለመታደግ የግልና የአካባቢን ንጽህናን መጠበቅ ወሳኝ ነው” ብለዋል፡፡

የደሴ ከተማ አስተዳደር የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አለባቸው ሰይድ በበኩላቸው “የጽዳት ዘመቻው የብልጽግና አመራሩ ከህብረተሰቡ ጋር በቅርበት ለመስራት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል”ብለዋል፡፡

ከፒያሳ በመናኸሪያ መናፈሻ፣ ከፒያሳ ተቋም፣ ከተቋም ቧንቧ ውሃን ጨምሮ በዋና ዋና መንገዶችና ቦታዎች የፅዳት ስራው ተከናውኗል።

የጽዳት ዘመቻው አመራሩ የብልጽግና ጉዞውን ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን ለማሳካት ለሚያደርገው ቀጣይ ስራ አመላካች መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በደሴ ከተማ የጽዳት ዘመቻ ላይ የተገኙት የደቡብ ወሎ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኤርሚያስ መኮንን ናቸው።


ከለውጡ ጋር እኩል የሚራመድ አመራር በቅንጅት ለመፍጠርም እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ከአጎራባች ክልሎችና ዞኖች ጋር በቅርበት መስራት መጀመሩ የቀጠናውን ሰላም ለማረጋገጥ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

በባህር ዳርና ደሴ ከተሞች በተካሄደው የፅዳት ዘመቻ ሁለተኛ ዙር ሰልጣኝ የብልጸግና ፓርቲ አመራሮችና የከተማው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም