የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ 2 ሺህ 883 ተማሪዎችን አስመረቀ

107

ሀረር፣  መስከረም 9/2013 (ኢዜአ) የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት ዘርፍ ያሰለጠናቸውን 2 ሺህ 883 ተማሪዎች በመጀመሪያ ፣ በሁለተኛና በዶክትሬት ድግሪ አስመርቋል።

በምረቃው ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ጀማል ዩስፍ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው ችግር ፈቺ በሆሩ የምርምር ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።

በአዝዕርት፣እንስሳት፣በጤና፣ እና ለሌሎች ምርምር ሲካሄዱ ከነበረባቸው 259 የምርምር ፕሮጀክቶች መካከል 109ኙ የተጠናቀቁ ሲሆን 150ዎቹ ደግሞ በሂደት ላይ እንደሚገኙም አብራርተዋል።

ኮቪድ 19ን ለመከላከል የሚረዱ 26 በሂደት ላይ ያሉና 4 የተጠናቀቁ የምርምር ፕሮጀክቶችም እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በማህበረሰብ አገልግሎት ዩኒቨርሲቲው በተለይ ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ በ100 ሚሊዮን ብር የሚገመት የምርመራ ላብራቶሪ ቁሳቁስ፣የምግብ እህል ድጋፍ እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ማከናወኑን ተናግረዋል።

በ2013 የትምህርት ዘመንም ዩኒቨርሲቲው ከሚያከናውነው የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት በተጓዳኝ ከኦሮሚያ ክልል ጋር በመተባበር በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ልዩ ችሎታ ያላቸውን 240 የዘጠነኛ ክፍል ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዩኒቨርሲቲው መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው ዘንድሮ ካስመረቃቸው ተማሪዎች መካከል 25ቱ በዶክትሬት ዲግሪ፣ 615ቱ በሁለተኛ ዲግሪና ቀሪዎቹ ደግሞ በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቁ ሲሆን ከተመራቂዎቹ መካከልም 21 በመቶው ሴቶች ናቸው።

ሀገሪቱ አልማ የተነሳችውን የሰለጠነ የሰው ሃይል ለማፍራት በመጀመርያ፣ሁለተኛና ዶክትሬት ድግሪ የትምህርት ክፍሎችን ወደ 200 ከፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

የእለቱ የክብር እንግዳና የምስራቅ ሐረርጌ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ሁሴን ፈይሶ በበኩላቸው ቀደምት ተማሪዎች ከሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ተመርቀው የወጡ ተማሪዎች ለአገራቸው ለወገኖቻቸውና ብሎም ለቤተሰቦቻቸው ታሪክ ሰርተዋል።

“ተመራቂ ተማሪዎች ይህን ተሞክሮ በማንገብ የመማር ባህላቸውን ይበልጥ ማዳበር አለባቸው ለዓላማቸው መሳካትና ለአገሪቱ ለውጥ ጠንክረው ሊሰሩ ይገባል”ብለዋል።

ከተመራቂዎቹ መካከል የግብርና ምጣኔ ሀብት በ3ኛ ድግሪ የተመረቀችው ዶክተር ሃይማኖት እሸቱ በበኩሏ በዚህ ወቅት በርካታ ችግሮችን ተቋቁማ ለምረቃ በመብቃቷ መደሰቷን ገልጻ፤ ሌሎችም ከዚህ ልምድ እንዲወስዱ ምክሯን ለግሳለች።

የውስጥ ደዌ እስፔሻሊስት ተመራቂ ዶክተር ማማሩ ታደሰ በበኩሉ እንደተናገረው የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ብዙ ሰዎች ንጽህና መጠበቅ ለምደዋል።

“ይህም ባህል ሆኖ እንዲቀጥል በህክምናውም በምርምር ስራ እና ተማሪዎችን በማብቃት ስራ የበኩሌን እወጣለው” በማለት ገልጿል።

በኢትዮጵያና አሜሪካ መንግስት ትብብር በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ1956 የተመሰረተው የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ከ100 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በዲፕሎማ በመጀመሪያ፣ሁለተኛና ዶክትሬት ድግሪ አሰልጥኖ አስመርቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም