አዲስ አበባን ፅዱና ውብ ለማድረግ የዘመቻ ስራ ብቻ በቂ አይደለም- ነዋሪዎች

127

አዲስ አበባ፣ መስከረም 9/2013 ዓ.ም ( ኢዜአ) አዲስ አበባን ፅዱና ውብ ለማድረግ የዘመቻ ስራ ብቻ በቂ አለመሆኑን ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የመዲናዋ ነዋሪዎች ተናገሩ።

ከተማችንን ውብ እና ለኑሮ የተመቸች ለማድረግ ፅዳት የሁላችንም የየእለቱ ክንውን መሆን ይኖርበታልም ብለዋል።

ህብረተሰቡ ስለ ፅዳት ያለው ግንዛቤ እየተሻሻለ ቢመጣም አሁንም ችግሮቹ እንደሚስተዋሉም ተገልጿል።

በአዲስ አበባ ዓለም አቀፉን የጽዳት ቀን በማስመልከት ዛሬ ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ የጽዳት ዘመቻ ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትም በከተማዋ የተወሰኑ ቦታዎች ተዘዋውሮ ባደረገው ምልከታ በፅዳት ላይ የነበሩ ሰራተኞችንና ነዋሪዎችን አነጋግሯል።

አስተያየት ሰጭዎቹ እንዳሉትም አዲስ አበባን ፅዱና ለኑሮ የተመቸች ለማድረግ የዘመቻ ስራ ብቻውን በቂ አይደለም።

ከተማችንን ውብ ለማድረግ ፅዳት የሁላችንም የየእለቱ ክንውን መሆን ይኖርበታልም ነው ያሉት።

ለከተማዋ መቆሸሽ ምክንያቱ የሁላችንም ግደለኝነትና ለፅዳት የምንሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆኑን የሚያመላክት መሆኑንም ገልጸዋል።

አዲስ አበባን ውብ የማድረግ ጥረቱ በየደረጃው የቁርጠኝነት ማነስ እንደሚስተዋልበት የመንገድ ፅዳት ሠራተኞቹ ገልፀዋል።

እንደ አስተያየት ሰጭዎቹ ገለፃ በብዙ ማህበረሰብ ዘንድ ስለ ፅዳት ያለው ግንዛቤ ለውጥ ቢታይበትም አሁንም መንገድ ላይ ቆሻሻ የሚጥሉ በርካቶች ናቸው።

የኮሮናቫይረስ መከሰትን ተከትሎ ለአፍና አፍንጫ መሸፈኛ የሚያገለግሎ ማስኮች በየስፍራው እየተጣሉ መሆኑም ለከተማዋ መቆሸሽና ለሰዎች የጤና እክል አይነተኛ ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል።

አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብና ፅዱ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የሁሉም አካላት ቁርጠኝነት የሚያስፈልግ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ዓለም አቀፉ የፅዳት ቀን በዛሬው እለት በዓለም ዙሪያ 190 አገሮች ተሳትፈውበት ተከናውኗል።

በበጎ ፈቃደኞች የሚከናወነው ይህ ዓለም አቀፍ ዘመቻ ሚሊዮኖችን በማስተባበር "ፕላኔታችንን እናፅዳ" በሚል መርህ ነው የተከናወነው።

በዛሬው መርሃ ግብርም በዓለም ዙሪያ ከ25 ሚሊዮን በላይ በጎ ፈቃደኞች እንደተሳተፉ ተገምቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም