ኢትዮጵያና ቻይና ሁለንተናዊ የሁለትዮሽ ግንኙነትን የሚያጠናክር ውይይት አደረጉ

105
አዲስ አበባ ግንቦት 2/2010 ኢትዮጵያና ቻይና ያላቸውን የሁለትዮሽና ሁለንተናዊ ግንኙነት የበለጠ ለማጎልበት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ውይይት አካሄዱ። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት ከቻይና ህዝባዊ ኮንግረስ ምክር ቤት አባላት ጋር ዛሬ ውይይት አድርገዋል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል እንደገለጹት ሁለቱ አገራት አዲስ አፈጉባኤ በሰየሙበት ወቅት የጋራ ምክክር መደረጉ ውይይቱን ልዩ ያደርገዋል። ኢትዮጵያና ቻይና የቀደምት ስልጣኔ ባለቤቶችና የራሳቸው ቋንቋ ያላቸው አገራት ቢሆኑም በተለያዩ ጊዜያት የሚፈልጉትን የኢኮኖሚና የልማት እድገት እንዳያስመዘግቡ የተለያዩ ተግዳሮቶች ሲያጋጥማቸው እንደነበር አስታውሰዋል። በአሁኑ ወቅት አገራቱ ከራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚጣጣም ፖሊሲና ስትራቴጂ ቀይሰው በመንቀሳቀሳቸው በኢኮኖሚና በልማት እድገት ስኬትን ማስመዝገብ መቻላቸውን ገልጸዋል። በተለይ ቻይና ባለፉት ዓመታት ባደረገችው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ አስደናቂ እድገት ማስመዝገቧን ጠቁመው፤ አገራቱ  ያላቸውን ግንኙነት የበለጠ እያጎለበቱ የሚሰሩባቸውን መስኮች አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል። ቻይና ኢትዮጵያ በሶማልያ፣ በደቡብ ሱዳንና በቀጠናው ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን የምታደርገውን ጥረት ድጋፍና እገዛ አጠናክራ እንድትቀጥልም ጠይቀዋል። የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ኬሪያ አብዱራህማን በበኩላቸው ቻይና በኢትዮጵያ እያደረገች ላለው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ቻይና በረጅም ጊዜ የሚከፈሉና ከወለድ ነጻ የብድር አገልግሎት በማቅረብ፣ በኢንቨስትመንት፣ በንግድ፣ በኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ፣ በኢትዮ ጅቡቲ የባቡር ሀዲድ ግንባታ፣ በአቅም ግንባታ፣ በጥናትና ምርምር፣ በአቪዬሽንና በቱሪዝም መስክ እያደረገች ያለውን ድጋፍም አጠናክራ እንድትቀጥል ጠይቀዋል። የቻይና ህዝባዊ ኮንግረስ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ሌ ዛን ሹን በበኩላቸው በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ሰላማዊ የሃላፊነት ሽግግርና ሁለት ሴቶች አፈ-ጉባኤ በሆኑበት ወቅት ጉብኝት ማድረጋቸው ታሪካዊ መሆኑን ተናግረዋል። አፈ- ጉባኤው ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በኢትዮጵያ ያደረጉት የመጀመሪያ ጉብኝት መሆኑንና ይህም ለሁለቱ አገራት ሁለንተናዊ ግንኙነት ቻይና ትልቅ ቦታና ትኩረት እንደምትሰጠው ማሳያ ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለው የኢኮኖሚ እድገት ለሌሎች የአፍሪካ አገራት ምሳሌ የሚሆን እንደሆነም ገልጸዋል። በቀጣይም ቻይና የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር መጠነ ሰፊ አገልግሎት እንዲሰጥ፣ በኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ፣ በኢንቨስትመንት፣ በአቅም ግንባታ፣ በነጻ የትምህርት እድልና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲጠናክር የምታደርገውን ጥረት ትቀጥላለች ብለዋል። ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ታዋቂ በሆነችበት በአትሌቲክስ ዘርፍም ቻይና በትብብር መስራት እንደምትፈልግ ነው አፈ-ጉባኤው የጠቆሙት። በሶማልያ እየተመዘገበ ያለው ሰላምና መረጋጋት ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንዲሁም በደቡብ ሱዳን ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ቻይና ከኢትዮጵያና ከአፍሪካ ህብረት ጋር በትብብር እንደምትሰራም አረጋግጠዋል። ከውይይቱ በኋላ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲሁም የቻይና ህዝባዊ ኮንግረስ ምክር ቤት በትብብር መስራት የሚያስችላቸውን የጋራ መግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል። ኢትዮጵያና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት በ1970 ዓ.ም ነው። ቻይና በኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች 4 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰሷንና ለ100 ሺህ ኢትዮጵያውያን ዜጎች የስራ እድል መፍጠሯን መረጃዎች ያመለክታሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም