የብር ኖት ለውጡ ኢኮኖሚውን ያነቃቃዋል- ምሁራን

103

ደሴ/ጎንደር/ሶዶ ፣ መስከረም 9/2013( ኢዜአ ) በኢትዮጰያውያ የተደረገው የብር ኖቶች ለውጥ ህገወጥ የገንዘብ ዝውውርና ሙስናንን በመከላከል ኢኮኖሚውን የሚያነቃቃው መሆኑን ምሁራን አስታወቁ።

የመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር ወንድሙ ረዳ ለኢዜአ እንደገለጹት መንግስት የብር ኖቶች እንዲቀየሩ ማድረጉና አዲስ ባለ 200 ብር ኖት መጨመሩ ኢኮኖሚውን ያነቃቃዋል።


ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ የሃሰተኛ ብር ማጭበርበር ጨምሮ ሙስናን ለመከላከል የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል ።


“የብር ኖት ለውጡን ተከትሎ ከባንክ ውጭ የተቀመጠ ገንዘብ ወደ ባንክ እንዲገባ መደረጉም ኢኮኖሚውን ለመታደግ ያግዛል” ብለዋል ።


ሌላው የኢኮኖሚክስ መምህር መብቱ መላኩ በበኩላቸው የተለያዩ የዓለም ሀገራት በየአስር ዓመቱ የብሮ ኖቶችን እንደሚቀይሩ ጠቅሰዋል ፡፡

“የብር ኖት ለውጡ የዘገየ ቢሆንም የተቀዛቀዘውን ኢኮኖሚ ያነቃቃዋል” ብለዋል።

“በሀገሪቱ አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አኳያም ሁከት፣ ብጥብጥና አለመረጋጋትን ለመቀነስ፣ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመግታት ያግዛል” ሲሉም ተናግረዋል።

በተለይም አዳዲስ የብር ኖቶቹ የደህንነት መጠበቂያ ምልክቶች ያሏቸው መሆናቸው ህገወጥ ተግባራትን ለመከላከል የሚያስችሉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል ።


 “መንግስት የብር ኖቶችን በመለወጥ የወሰደው እርምጃ ተገቢና ወቅቱን የጠበቀ ነው” ያሉት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጥናትና ምርምር ዳይሬክተርና የማኔጅመንት መምህር አቶ አብዱሮህማን አወል ናቸው።

ኢኮኖሚውን ለማነቃቃትና ህገ ወጥ ተግባራትን ለመከላከል ጠቀሜታው የላቀ መሆኑን አስታውቀዋል ።


“በኢትዮጵያ የገንዘብ ዝውውር ይታዩ የነበሩ ጤናማ ያልሆኑ ተግባራት በአዲሶቹ የብር ኖቶች እንዳይደገሙ መንግሰት የተጠናከረ የገንዘብ ፖሊሲ ሊተገብር ይገባል” ያሉት ደግሞ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት ምሁርና የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዶክተር ፈንታሁን ባዬ ናቸው።


ባለፉት አመታት ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርና ጤናማ ያልሆነ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር የተወሰዱ እርምጃዎች በገንዘብ ፖሊሲው ደካማነት ውጤት ሳያመጡ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል፡፡


የገንዘብ ፖሊሲው ደካማ መሆን የኑሮ ውድነት፤ የዋጋ ግሽበትና የብር የመግዛት አቅም ማሽቆልቆል እንዲስተዋል ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል ።

መንግሰት አዲስ የገንዘብ ኖቶችን ማሳተሙ በኢኮኖሚ ውስጥ የሚታዩ ህገ-ወጥ ተግባራትን ለመቆጣጠር እንደሚያስችል አመላክተዋል።

የዩኒቨርሲቲው የአካውንቲንግና ፋይናንስ መምህር ዶክተር ሳሙኤል አለምነው በበኩላቸው አዲሶቹ የብር ኖቶች በገበያ ውስጥ የሚታየውን ህገ-ወጥ የገንዘብ ፍሰትና ዝውውር ለመቆጣጠር አጋዥ እንደሚሆኑ ተናግረዋል ።


“አንድ ኢኮኖሚ እራሱን የቻለ ገንዘብ የመሸከም አቅም አለው” ያሉት ዶክተር ሳሙኤል በኢትዮጵያ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውሩ ጤናማ ኢኮኖሚ እንዳይኖር እንቅፋት ፈጥሮ መቆየቱን አውስተዋል። 

“ከአዲሶቹ የብር ኖቶች ለውጥ በኋላ ተመሳሳይ ችግር እንዳያጋጥም መንግሰት የገንዘብ ፖሊሲውን በማጠናከር ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር እንዲገታ ተገቢውን እርምጃ ሊወስድ ይገባል” ብለዋል፡፡ 

“የብር ኖት ለውጡን ተለትሎ በግለሰቦች እጅ አላግባብ የተከማቹ ገንዘቦች ወደ ባንክ እንዲመጡ መደረጉ ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት ፋይዳቸው የጎላ ነው “ያሉት ደግሞ የኢኮኖሚክስ መምህር ዶክተር ተፈሪ በሪሁን ናቸው፡፡

ነባሮቹን የገንዘብ ኖቶች በአዲስ የመተካቱ ሂደት በህገ-ወጥ መንገድ የተከማቹ ገንዘቦች አላግባብ እዳይለወጡ ኃላፊነት የሚሰጣቸው የህግ አስፈጻሚ አካላት ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል ሊያደርጉ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

የወላይታ ሶዶ ነዋሪዎችም መንግስት በብር ኖት ላይ ያደረገው ለውጥ ሀሰተኛ የገንዘብ ዝውውርን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንደሚያስችል ተናግረዋል ።


የብር ኖት ለውጡ ለህገ ወጥ እንቅሰቃሴዎች የሚደረግን ድጋፍ፣ ሙስናና ኮንትሮባንድን ለመቆጣጠር እንዲያግዝ ነዋሪዎቹ ጠቅሰዋል ።

የሶዶ ከተማ ነዋሪ አቶ ስመኘው ዳና አዳዲስ የብር ኖቶች ላይ የተደረጉት የደኅንነት ገጽታዎች ሀሰተኛ የገንዘብ ዝውውርን ለመከላከል ጠቀሜታ እንዳላቸው አመላክተዋል ።


በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የወላይታ ሶዶ ዲስትሪክት ባልደረባ አቶ ሕዝቄል ብርሃኑ በበኩላቸው 

ሀሰተኛ የብር ኖቶች ዝውውር ለመቆጣጠር የተወሰደው እርምጃ የፋይናንስ ተቋማትን የገንዘብ እጥረት ለመቅረፍ አጋዥ እንደሆነ አስታውቀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም