ምክር ቤቱ አገራዊ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ላይ የውሳኔ ሀሳብ እንዲያቀርቡ ለቋሚ ኮሚቴዎች መራ

38

አዲስ አበባ፣ መስከረም 8/2013 (ኢዜአ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አገራዊ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምላሽና ቀጣይ እርምጃዎችን አስመልክቶ ከጤና ሚኒስቴር በቀረበ ምክረ ሀሳብ ላይ የውሳኔ ሀሳብ እንዲያቀርቡ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መራ።

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው አምስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሦስተኛ አስቸኳይ ስብሰባው ከጤና ሚኒስቴር በቀረበለት ሪፖርት ላይ ተወያይቷል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምላሽና ቀጣይ እርምጃዎች ላይ ያተኮረ ሪፖርትና ምክረ ሀሳብ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።

ዶክተር ሊያ አጠቃላይና ዝርዝር ምክረ ሀሳቦችን ያቀረቡ ሲሆን ትምህርት ቤቶችን ስለመክፈትና አገራዊ ምርጫን ማካሄድን በተመለከተም በዝርዝር አቅርበዋል።

ወረርሽኙን ለመከላከል እየተወሰዱ ያሉ የጥንቃቄ እርምጃዎችን በአግባቡ በመተግበር ትምህርት ቤቶች ቢከፈቱ የሚል ምክረ ሀሳብ አቅርበዋል።

ትምህርት ለመጀመር ከመወሰኑ በፊት ግን ጠንካራ ግብረ ኃይል በየደረጃው ተቋቁሞ ወደ ሥራ መገባት እንዳለበት ሚኒስትሯ አስታውቀዋል።

አገራዊ ምርጫ ማካሄድን በተመለከተም ከዚህ በፊት ከነበሩ ምርጫዎች በተለየ መልኩ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን መከላከል ከግምት ያስገቡ ቅድመ ሁኔታዎችን አሟልቶ ምርጫ ማካሄድ እንደሚቻል ምክረ ሀሳብ አቅርበዋል።

ምክር ቤቱ በቀረበው ምክረ ሀሳብ ላይ ውይይት ካደረገ በኋላ በዋናነት ለሴቶች፣ ወጣቶችና ማኅበራዊ ቋሚ ኮሚቴና ለሕግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የውሳኔ ሀሳብ እንዲያቀርቡ መርቷል።