በሚሌኒየም አዳራሽ የኮቪድ-19 ማዕከል እስካሁን ድረስ የ64 ሰዎች ህይወት አልፏል

132

አዲስ አበባ ፣መስከረም 8/2013 (ኢዜአ) በሚሌኒየም አዳራሽ የኮቪድ-19 ማዕከል እስካሁን ድረስ የ64 ሰዎች ህይወት ማለፉን ማዕከሉ ገለጸ። ማህበረሰቡ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ አደገኛ መሆኑን በመገንዘብ ጥንቃቄ ከማድረግ እንዳይዘናጋ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።

በሚሌኒየም አዳራሽ የኮቪድ-19 ማዕከል በግንቦት ወር 2012 ዓ.ም የኮሮናቫይረስ ህሙማንን ተቀብሎ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ይታወቃል።

የማዕከሉ ሃላፊ ዶክተር እስማኤል ሸምሰዲን ማዕከሉ ስራውን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ ትናንት ጠዋት በነበረው መረጃ 2 ሺህ 961 ህሙማን አገልግሎት ማግኘታችውና ከነዚህም ውስጥ 64 የሚሆኑት ህይወታቸው ማለፉን ለኢዜአ ገልጸዋል።

2 ሺህ 385 ሰዎች ደግሞ አገግመው ከማዕከሉ መውጣታቸውን ነው ዶክተር እስማኤል ያስረዱት።

ባለፈው ሶስት ሳምንት ገደማ በኮሮናቫይረስ የሟቾች ቁጥር በእጥፍ መጨመሩንና ይሄም በጣም አሳሳቢ እንደሆነ ተናግረዋል።

የሟቾች ቁጥር መጨመር ብቻ ሳይሆን የጽኑ ታማሚዎች ቁጥርም እየጨመረ መምጣቱንና በማዕከሉ አሁን ያሉት ታማሚዎች ሁሉም በመተንፈሻ መርጃ መሳሪያ ድጋፍ እንደሚገኙ አመልክተዋል።

በአሁኑ ሰአት 200 ህሙማን በሚሊኒየም አዳራሽ የኮቪድ-19 ህክምና ማዕከል እንደሚገኙ አመልክተዋል።

የኮሮናቫይረስ ሳይኖርባቸው ለሌሎች ህክምናዎች የመጡ 88 ህሙማን  ወደ ሌላ የህክምና ማዕከል እንዲላኩ መደረጉን ገልጸዋል።

224 ቀላልና መካከለኛ የቫይረሱ ምልክት ያለባቸው ህሙማን ወደ ሌላ የህክምና ማዕከል እንዲዘዋወሩ መደረጉን ተናግረዋል።

የሚሌኒየም አዳራሽ የኮቪድ-19 ህክምና ማዕከል በአሁኑ ሰአት ጽኑ ታማሚዎችና በተጓዳኝ ህመማቸው በቫይረሱ ምክንያት ለከፍተኛ ህመም የተጋለጡ ህሙማንን አገልግሎት እየሰጠ እንደሆነ አመልክተዋል።

ማህበረሰቡ ነገን ለማየት ራሱን ከኮሮናቫይረስ በመጠበቅ የራሱንም ሆነ የሌሎችን ህይወት መታደግ እንደሚገባው ነው ዶክተር እስማኤል ያሳሰቡት።

የሚሊኒየም አዳራሽ የኮቪድ-19 ማዕከል እስከ 1 ሺህ 200 ህሙማንን የማስተናገድ አቅም አለው።

እስከ ትናንት ማምሻውን ባለው መረጃ በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 66 ሺህ 913 የደረሰ ሲሆን 1 ሺህ 60 ሰዎች ህይወታቸው አልፏል።

27 ሺህ 85 ሰዎች ከቫይረሱ ያገገሙ ሲሆን በአሁኑ ሰአት ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች ቁጥር ደግሞ ወደ 38 ሺህ 766 ከፍ ብሏል።

በኢትዮጵያ እስካሁን 1 ሚሊዮን 176 ሺህ 252 የላብራቶሪ ምርመራ ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም