ስለአዲሱ የብር ኖቶች ለህብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል---የባንክ ደንበኞች

71

አዲስ አበባ፣ መስከረም 8/2013(ኢዜአ) ወደ አገልግሎት የገቡ አዳዲስ የብር ኖቶችን መጠንና ቀለም ህብረተሰቡ በደንብ እስኪያውቅ ድረስ በተከታታይ ማስተማር እንደሚገባ የባንክ ደንበኞች ተናገሩ።

ኢትዮጵያ ነባሮቹን የ10፣ የ50 እና የባለ 100 ብር ኖቶችን መቀየሯ እንዲሁም አዲስ ባለ 200 ብር ኖት ወደ ሥራ ማስገቧቷን በቅርቡ መንግስት ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው።

ኢዜአ የነዚህን የብር ኖቶች የቅያሬ አገልግሎት አስመልክቶ በተወሰኑ ባንኮች በመዘዋወር የባንክ ደንበኞችን አነጋግሯል።

የባንኮቹ ደንበኞች እንዳሉት፣ ባንኮች ከሚሰጡት የገንዘብ ኖቶች ቅያሬ አገልግሎት ጎን ለጎን ከደንበኞቻቸው ጋር ባላቸው ግንኙነት ስለ አዲሶቹ የብር ኖቶቹ መጠንና ቀለም ለደንበኞቻቸው ግንዛቤ በመፍጠር ማሳወቅ ይኖርባቸዋል።

አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል የአዋሽ ኢንተርናል ባንከ ደንበኛ አቶ ህልሜ ኑርልኝ ባንኮቹ በተለይ በገጠሩ ማህበረሰብ ላይ አተኩረው እንዲሰሩ ተናግረዋል።

ለደንበኞቻቸው የብር ኖቶችን ቀለም በአግባቡ ቢያስተዋውቁና ህብረተሰቡ በገንዘብ ቅያሬና ልወውጡ ወቅት ሊፈጠርበት የሚችለውን የመጭበርበር ስጋት ለመቀነስ ቢሰሩ መልካም መሆኑን ይገልጻሉ።

በዳሽን ባንክ አዲሱን የብር ኖቶች ሲቀይሩ ያገኘናቸው ወይዘሮ ቅድስት መልኬ እና አቶ መታሰቢያ ምስራቅ ደግሞ የብር ኖቶቹን በመጠንና በቀለም መለየት አዳጋች መሆኑን ነው የተናገሩት።

“ቤተሰቦቼ ስለአዲሶቹ ብሮች ግንዛቤ እንዲኖራቸው በሚል ገንዘብ ከባንክ አውጥቺያለሁ” የሚሉት ወይዘሮ ቅድስት ህብረተሰቡ በቅያሬ ወቅት ግራ እንዳይገባውና ሲገበያይም መታለል እንዳይደርስበት ግንዛቤ የመፍጠር ስራው በትኩረት ልሰራ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የእሳቸውን ሀሳብ የሚጋሩት አቶ መታሰቢያም ሰዎች በአዲሶቹ የብር ኖቶች መጭበርበር እንዳይደርስባቸውና ዋጋቸውን በአግባቡ አውቀው መጠቀም እንዲችሉ በመገናኛ ብዙሀን ተከታታይ የማስተዋወቅ ሥራ መስራት እንዳለበት ገልጸዋል።

የዳሽን ባንክ ዋና ሥራአስፈጻሚ አቶ አስፋው አለሙ በበኩላቸው ስለአዳዲሶቹ የብር ኖቶች ህብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው በማድረግ በኩል በተለይ ከባንኮችና ከመንግስት ብዙ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።


ለዚህም በባንኩ ቅርንጫፎች ሁሉ ስለገንዘብ ኖቶቹ ለሠራተኞቻቸው በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው መደረጉን ገልጸው፣ በአሁኑ ወቅትም የባንኩ ሠራተኞችም ደንበኞችን ስለ ብር አይነቶቹ የማስተዋወቅ ሥራ መጀመራቸውን አመልክተዋል።

አቶ አስፋው እንዳሉት የግንዛቤ ፈጠራ ሥራው የገጠሩንና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በበቂ ሁኔታ ተደራሽ በማድረግ በኩል ግን ክፍተት ይኖራል የሚል ስጋት አለ።

በገንዘብ ቅያሬው ወቅት ደንበኞች በብዛት ወደባንኩ ሲመጡ ለኮሮናቫይረስ እንዳይጋለጡ በባንኩ በኩል ዝግጅት መደረጉን የተናገሩት ደግሞ የአዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ ምክትል ሥራአስኪያጅ አቶ ገመዳ ለማ ናቸው።

ከብር ኖቶቹ ቅያሬ ጋር በተያያዘ ስህተት እንዳይፈጠርም ለባንኩ ሠራተኞች አስቀድሞ ስልጠና ሲሰጥ መቆየቱን አስረድተዋል።


የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መረጃ እንደሚያሳየው በአሁኑ ወቅት 2 ነጥብ 9 ቢሊዮን የብር ኖቶች ታትመው በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ለቅያሬ እንዲሰራጩ ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ በቅርቡ በሰጡት መግለጫ የብር ቅያሬውን ለማከናወን ማንኛውም ግለሰብ የብር ኖቶቹን ራሱ ባንክ ሄዶ መቀየር እንዳለበት መግለጻቸው ይታወሳል።


የብር ለውጡን ተከትሎ ህገ ወጥ ተግባራትን ለመቆጣጠር ዝግጅት ተደርጓል።

የብር ኖቶቹ መቀየር መንግስት በኢትዮጵያ ውስጥ እየተንቀሳቀሰ ያለውን የገንዘብ መጠንና ምንጮች ለማወቅና ለመቆጣጠር እንደሚያስችለው ተመልክቷል።


ህጋዊ ያልሆነው ገንዘብ ወደ ህጋዊው የፋይናንስ ስርአት ውስጥ እንዲገባ በማድረግ በባንኮች የሚኖረውን ተቀማጭ ገንዘብ መጠን እንደሚያሳድግም የምጣኔ ሀበት ባለሙያዎችም ይገልጻሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም