በኢትዮጵያ ከ1 ሺህ 300 በላይ የጤና ባለሙያዎች በኮሮናቫይረስ ተይዘዋል

48

አዲስ አበባ፣መስከረም 6/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ ከ1 ሺህ 300 በላይ የጤና ባለሙያዎች በቫይረሱ መያዛቸውን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ በነገው ዕለት የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የሕሙማን ደህንነት ቀንን አስመልክቶ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫውን የሰጡት የሚኒስቴሩ የሕክምና አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ያዕቆብ ሰማን እንዳሉት ኮሮናቫይረስን  በመከላከል ሥራ ግንባር ቀደም የሆኑ የሕክምና ባለሙያዎች ላይ መጠነ ሰፊ ችግር አስከትሏል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በኮቪድ-19 ከተያዙ ሰዎች መካከል 1 ነጥበ 3 ሚሊዮን የሚሆኑት የጤናው ሴክተር ሠራተኞች ናቸው።

"በኢትዮጵያም ኮቪድ-19 ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ 1 ሺህ 311 የሚሆኑ የጤና ባለሙያዎች በቫይረሱ ሲያዙ 700 የሚሆኑት ደግሞ አገግመው ወጥተዋል፤ ቀሪዎቹ  በህክምና ተቋማት ይገኛሉ" ብለዋል አቶ ያዕቆብ።

ሁለት የሕክምና ባለሙያዎችም ለሞት መዳረጋቸውን ነው ያስታወሱት።

ነገ ለሁለተኛ ጊዜ በአገሪቱ የሚከበረው የሕሙማን ቀንም በቫይረሱ የተያዙ ወገኖቻቸውን ሌት ተቀን እያገለገሉ ላሉ ባለሙያዎችና አጋሮቻቸው ክብርና ምስጋናን በመስጠት እንደሚከበር ተናግረዋል።

በዓሉ የጤና ባለሙያዎች በሥራ ላይ የሚገጥማቸውን ችግር በመፍታትና በማገዝ እንዲሁም ራሳቸውን ከበሽታ ጠብቀው ህዝባቸውን እንዲያገለግሉ በሚያደርጉ ፕሮግራሞች የሚከበር መሆኑንም ነው አቶ ያዕቆብ ያመለከቱት።

የጤና ባለሙያዎች ደህንነት እንዲጠበቅ የሚያስችል ሳይንሳዊ የሆኑ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው የሚመለከታቸው አካልት እንዲወያዩበት የሚደረግበት መሆኑንም ጠቁመዋል።

"በተጨማሪ በዓሉ በቫይረሱ የተጠቁ የሕክምና ባለሙያዎችና ሠራተኞችን በመጠየቅና በማበረታታ ይከበራል" ብለዋል።

ህብረተሰቡም የጤና ባለሙያዎች ደህንነታቸው እንዲጠበቅ የሕክምና ቁሶችን ባለማባከንና በማበረታታት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የሕክምና እቃ እቅራቢዎችም በአስቸጋሪ ወቅት ለባለሙያዎቹ የሚያስፈልጉ ቁሶችን በአግባቡ በማቅረብ አብሮነታቸውን በተግባር ማሳየት እንደሚገባቸው አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም