አገር በቀል የምጣኔ ሃብት ማሻሻያ ትግበራን የሚያሳልጡ የቴክኖሎጂ ሽግግር ዲፕሎማሲ ያስፈልጋል-ሚኒስትር ገዱ

65

አዲስ አበባ መስከረም  5/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ እየተገበረች ያለውን አገር በቀል ምጣኔ ሃብት ማሻሻያ ትግበራን የሚያሳልጡ የቴክኖሎጂ ሽግግር ዲፕሎማሲ ላይ ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው አሳሰቡ።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ኢትዮጵያን በተለያዩ አገሮች ከወከሉ አምባሳደሮችና የቆንስላ ጄኔራሎች ጋር በቴክኖሎጂ ዘርፍ በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ላይ መክሯል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በዚሁ ወቅት ለአንድ አገር ሁለንተናዊ እድገትና ብልጽግና የሳይንስና ቴክኖሎጂ ግኝቶችን አስተዋጽኦ አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የያዘችውን የብልጽግና ጉዞ የሚያግዝ ቴክኖሎጂ ከአገራዊ የምጣኔ ሃብት እድገትና ፍላጎት በመነሳት ማፈላለግና ማቅረብ የዲፕሎማሲ ሥራ ተልዕኮ መሆኑንም ገልጸዋል።

ከምጣኔ ሃብት ዲፕሎማሲ ሥራዎች መካከልም የቴክኖሎጂ ሽግግር መስክ አንዱ መሆኑንም  አመልክተዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለውን የአገር በቀል የምጣኔ ሃብት ትራንስፎርሜሽን ለማገዝ የቴክኖሎጂ ሽግግር ዲፕሎማሲ ማከናወን ያስፈልጋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብት ልማትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ እምየ ቢተው በበኩላቸው ኢትዮጵያ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያጸደቀቻቸውን ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ለዓለም ማሳወቅ ያስፈልጋል ብለዋል።

ዘርፉ ሥራ በመፍጠር፣ ገቢ በማመንጨትና የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል ያለውን ፋይዳ በመረዳት አዳዲስ የፈጠራ ውጤቶችን ወደ አገር ማምጣት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

በቴክኖሎጂ የበለጸጉ አገሮች  በስልጠና፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በሌሎች ከዘርፉጋር ባለው እንቅስቃሴ ከኢትዮጵያ ጋር እንዲሰሩ በዲፕሎማሲው መስክ ጥረት እንዲደረግ ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለውን የለውጥ ሂደት ለመደገፍ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተያዙ አቅጣጫዎች ላይ ገለጻ ያደረጉት ደግሞ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ ናቸው።

በመሆኑም ሃብት በማፈላለግ፣ በዘርፉ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብና ተያያዥነት ባላቸው ዘርፎች ዲፕሎማቶች እንዲያግዙ ጠይቀዋል።

በመድረኩ ለአምባሳደሮችና የቆንስላ ጀነራሎች የሚኒስቴሩ የ10 ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ ገለጻ ተደርጎላቸዋል።

ዕቅዱ የዲፕሎማቶችን ተሳትፎ በሚጠይቀው አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ትብብር መፍጠር አንደኛው ግብ ነው ተብሏል።

የአገር በቀል ምጣኔ ሃብት ሽግግርን ታሳቢ በማድረግ በተዘጋጀው ዲጂታል ስትራቴጂን አካታች በሆነው የኢትዮጵያ ብልጽግና ላይም ገለጻ ተደርጓል።ውይይትም አደርገዋል።

ኢትዮጵያን በውጭ የሚወክሉ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች በቢሾፍቱ ከተማ ለሁለት ሳምንታት የቆየ ስልጠና ማድረጋቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም