የጥቃቅንና አነስተኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዞች ምርቶቻቸውን እንዲያሳድጉ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

227

አዲስ አበባ፣ መስከረም 5/2013 ( ኢዜአ) የጥቃቅንና አነስተኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዞች ምርቶቻቸውን የማሳደግ ዓላማ ያለው የገንዘብ ድጋፍ ስምምነት ተደርጓል።

በኢትዮጵያ ንግድ እና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት፣ ፕሪሳይስ ኢንተርናሽናል ኮንሰልታንትና የፈጠራ ድርጅት እንዲሁም የግሪን ኢትዮጵያ ማኑፋክቸሪንግ ፕሮጀክት ተጠቃሚ ኢንተርፕራይዞች መካከል ነው የገንዘብ ድጋፍ ስምምነቱ የተደረገው።

ስምምነቱን የኢትዮጵያ ንግድ እና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ጸሐፊ አቶ የሱፍ አደምኑር ፕሮጀክቱ ኢንተርፕራይዞች ጋር ተፈራርመዋል።

ይህ የማበረታቻ ድጋፍ በኢትዮጵያ ያሉ የጥቃቅንና አነስተኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንተርፕራይዞች የተለያዩ ማሻሻያዎችን በማድረግ  ምርቶቻቸውን እንዲያሳድጉ የማበረታታት ዓላማ አለው ተብሏል።

በተጨማሪም ድጋፉ በአምራች ዘርፍ ውስጥ የማያቋርጥ አፈጻጸም እና ቀጣይነት ያለው መሻሻል እንዲኖር ያደርጋል።

በገንዘብ ድጋፉ ተጠቃሚ የሆኑት በጨርቃ ጨርቅ፣ በቆዳ እና በእጅ ሥራ የተሰማሩ የጥቃቅን እና አነስተኛ አምራች ድርጅቶች እንደሆኑ ተገልጿል።

ድርጅቶቹ የገንዘብ ድጋፍ ስምምነት ያደረጉት ሃብትን በመቆጠብ፣ ከአየርና ከውሃ ብክለት ነጻ በሆነ መንገድ እና ፈጠራን መሰረት ባደረገ  መልኩ ቴክኖሎጂን በመጠቀም  ማምረት በመቻላቸው እንደሆነ ተመልክቷል።

ስምምነቱን ያደረጉት በጥቃቅን እና አነስተኛ አምራች ድርጅቶች የተሰማሩ 11 ድርጅቶች እንደሆኑ የግሪን ኢትዮጵያ የማኑፋክቸሪንግ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ኽይሩ ሐሰን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ እና የዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት  ጸሐፊ አቶ የሱፍ አደምኑር መርሃ- ግብሩ እንዲሳካ ድጋፍ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

የገንዘብ ድጋፉ ለተፈለገው ዓላማ እንዲውል ኢንተርፕራይዞቹ በትኩረት መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ግሪን ኢትዮጵያ ማኑፋክቸሪንግ ፕሮጀክት በኢትዮጵያ ያሉ አነስተኛ እና ጥቃቅን አምራች ኢንዱስትሪዎች  ዘላቂ  በሆነ መንገድ  ምርቶቻቸውን እንዲያቀርቡ እና የአረንጓዴ ልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚደግፍ መርሃ-ግብር ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም