የአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የኮቪድ 19 ምርመራ ጀመረ

97

መቐለ (ኢዜአ) መስከረም 05/2013 ዓ/ም የዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የኮቪድ-19 ምርመራ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን አስታወቀ።

ምርመራው የተጀመረው በውጭ የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች ባደረጉት የስድስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ በተሟላ ላቦራቶሪ መሆኑም ተገልጿል።

የኮሌጁ ዲንና የምርመራ ማእከሉ ኃላፊ ዶክተር ሐየሎም ካህሳይ ለኢዜአ እንደገለጹት ከትናንት በስቲያ ስራውን በይፋ የጀመረው ማእከሉ በቀን እስከ አንድ ሺህ 500 ሰዎችን የመመርመር አቅም አለው።

ማዕከሉ በአሁኑ ሰዓት 18 የጤና ባለሙያዎች ተመድበውለት የምርመራ ስራ እያከናወኑ እንደሚገኙም አስረድተዋል።

ኮሌጁ ህሙማንን ለማከም የሚያስችል 80 አልጋዎችን ማዘጋጀቱን ገልጸው በቀጣይም የዩኒቨርሲቲው አንደኛና ሁለተኛ ዲግሪ የህክምና ተማሪዎች ተጨማሪ ምርምር ለማድረግ የሚጠቀሙበት እንደሆነም ተናግረዋል።

"ለኮቪድ-19 መመርመሪያ ተብሎው የተገዙ ሁለቱም የህክምና ማሽኖች በክልል ጤና ቢሮ እና ነዋሪነታቸውን ሰሜን አሜሪካ ባደረጉ የትግራይ ክልል ተወላጆች ትብብር ነው"ብለዋል።

የህክምና መሳሪያዎችና ሌሎች ቁሳቁሶች ለዩኒቨርሲቲው ያስረከቡት በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ የክልሉ ተወላጆችን ወክለው የቀረቡት አቶ ቴድሮስ ካህሳይ እንዳሉት፣ህብረተሰቡ ቫይረሱን ለመግታት መከላከልን መሰረት ያደረገ የጤና ፖሊሲ ተግባራዊ ሊያደርግ ይገባል።

ተወላጆቹ የጀመሩትን ድጋፍ በቀጣይም አጠናክረው እንደሚቀጥሉበት አስታውቀዋል።

በምርመራ ማዕከሉ ከተመደቡ የጤና ባለሙያዎች መካከል ሲስተር ርሻን ስባጋድስ እንዳሉት፣ለ24 ሰዓታት ህብረተሰቡን በሙያቸው ለማገልገል ዝግጁ ናቸው።

የቫይረሱን ስርጭት በመግታት ረገድም የህብረተሰቡ ቸልተኝነት መስተካከል እንዳለበት ጠቁመው የጤና ባለሙያዎችን በማገዝም የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ አሳስባዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም