ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር ተወያዩ

64

አዲስ አበባ መስከረም  5/2013 (ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከተለያዩ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር ተወያዩውይይቱ ከዚህ ቀደም ተካሂደው የነበሩትን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሁለት መድረኮችን ለመገምገም እና ቀጣይ የውይይት አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያለመ ነው።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሙሳ አደም፤ ቀደም ሲል ተካሂደው በነበሩ ሁለት የውይይት መድረኮች የነበሩ ጠንካራ እና ደካማ ጉዳዮችን አንስተዋል።

ሁሉን አቀፍ ብሄራዊ መግባባት ያስፈልጋል ያሉት ሰብሳቢው፤ በየክልሎቹ ያለው የፖለቲካ ምህዳር ጥራት፣ ህገ መንግስት፣ ፌዴራሊዝም እና ምርጫ ላይ ያተኮሩ ውይይቶች ከዚህ ቀደም መካሄዳቸውንም ጠቅሰዋል።

በዚህም ያለፉት መድረኮች ውጤታማ ነበሩ ያሉት አቶ ሙሳ፤ ብሔራዊ ምክክርና ውይይቶች እንዲካሄዱ መልካም አጋጣሚ የፈጠሩ ነበሩ ብለዋል።በምክር ቤቱ የመግባቢያ ሰነድ ስለመኖሩና በውይይት አጀንዳዎች ላይ በፓርቲዎቹ መግባባት መኖሩን አመራሮቹ በውይይቱ ወቅት አንስተዋል።

የፓርቲዎቹ አመራሮች በቀጣይ መድረክ መታየት ይገባቸዋል ያሏቸውን አንኳር ጉዳዮችም አንስተዋል።በተለይም ምርጫን በተመለከተ ሂደቱን ለማከናወን የሚችሉ ጠንካራ ተቋማትን ከመፍጠር አንፃር ቀጣይ የውይይት አጀንዳ ቢሆን ሲሉ አንስተዋል።አሁን ባለው ሁኔታ "ፓርቲ የሆነው እና ያልሆነው" የሚለውን ጉዳይ መረዳት በሚያስችሉ ጉዳዮችም ላይ ጠንካራ ውይይት ያስፈልጋል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በውይይቱ ወቅት እንዳሉት ተመሳሳይ ሃሳብ ያላቸው ፓርቲዎች ሰብሰብ ብለው በአንድ ላይ ቢሆኑና ቢጠናከሩ ሲሉ አንስተዋል።ከፓርቲዎች አደረጃጀት፣ ከወቅቱ የአገሪቱ የተቃርኖ ምንጮች እና ከምርጫ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይ ሰፋ ባላ ሁኔታ በጋራ ምክር ቤቱ ውይይት ማድረግም አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮቹ በሚቀጥለው ጊዜ ምን ይደረግ በሚሉ ጉዳዮች ላይ ተወያይተው የተለያዩ አራት ርእሰ ጉዳዮችን መርጠዋል።

ህገ መንግስት እና ህግ መንግስታዊነት ስር በዋናነት የቅራኔ ምንጮችን መለየት፣ የፖለቲካ አደረጃጀቶች ምን መምሰል እንዳለባቸው፣ ትክክለኛ ምርጫ ምን ማለት ነው በሚሉ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት የጋራ መግባባት ፈጥረዋል።

ፓርቲዎቹ ለመወያየት በመረጧቸው ጉዳዮች ላይ የመነሻ ፅሁፍ የሚያቀርቡ አራት የተለያዩ የፓርቲ አባላት ተመርጠዋል።በዚህም መሰረት ቀጣይ የውይይት መድረክ በሚቀጥለው ሳምንት ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም