በምዕራብ ኦሮሚያ ያለውን ሰላም ለማጠናከር በትኩረት ይሰራል

55

ነቀምቴ፣ መስከረም 4/2012 (ኢዜአ) በምዕራብ ኦሮሚያ ያለውን ሰላምና መረጋጋት በተያዘው ዓመትም አጠናክሮ ለማስቀጠል በትኩረት እንደሚሰራ የየአካባቢው አስተዳደሮች ገለጹ።

የምሥራቅ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አስመራ ኢጃራ ለኢዜአ እንደተናገሩት በአካባቢው ሠላም እንዲሰፍን ከህብረተሰቡ ጋር ቅንጅት በመፍጠር በተከናወኑ ስራዎች አበረታች  ውጤቶች ተመዝግበዋል።

የህግ የበላይነት የሰፈነበትና ህዝቡ ያለምንም ስጋት በሰላም ወጥቶ የሚገባበት ዞን ለማድረግ በተለይም ከወረዳ በታች ያለውን አደረጃጀት ለማጠናከር  እንሰራለን ብለዋል፡፡

በቄለም ወለጋ ቀደም ሲል  በነበረው ጸጥታ ችግር በሰው ህይወት ላይ ጉዳት ሲደርስ መቆየቱን የተናገሩት ደግሞ የዞኑ የአስተዳደርና የፀጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተፈሪ አሰፋ ናቸው፡፡

የነበረውን  የሠላም መደፍረስ ሁኔታ ለመመለስ ህዝቡ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር ተቀናጅቶ አካባቢውን በመጠበቅና የጥፋት ኃይሎችን አጋልጦ በመስጠት ባደረገው ተሳትፎ ዞኑ አሁን  በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ይህንን ሰላም አጠናክሮ ለማስቀጠልና የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ ዕቅድ አዘጋጅተው ከህብረተሰቡና ባለድርሻ አካላት ጋር እየተናበቡ ለመፈጸም መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡

በዞኑ ሰላምን በማወክ ተሳትፎ አላቸው ተብለው ከተያዙ 22 ተጠርጣሪዎች መካከል ዘጠኝ  ሰዎች ለሕግ መቅረባቸውን አመልክተው ስድስት በጊዜ ቀጠሮ ላይ እንደሚገኙና ቀሪዎቹ በማስጠንቀቂያ መለቀቃቸውን ጠቅሰዋል፡

የሆሩ ጉዱሩ ወለጋ ዞን የአስተዳደርና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ ፈይሣ  በበኩላቸው በአካባቢው  አሁን ያለው ሰላም ቀጣይነት እንዲኖረው ለማስቻል   ዕቅድ አዘጋጅተው ለመተግበር እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

ይህም የዞኑ ህዝብ ከፀጥታ አካላት ጋር ቅንጅት በመፍጠር አካባቢውን በመጠበቅ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በትኩረት እንዲሰራ የተመቻቸ መሆኑን አመልክተዋል።

በምዕራብ ወለጋ ዞን  የአስተዳደርና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ እንዳለ ወጋሪ በዞኑ አሁን የሰፈነውን ሰላም ለማረጋገጥ ዘንድሮ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በነቀምቴ ከተማ ተፈጥሮ ከነበረው የሠላም መደፍረስ ጋር ተያይዞ  አመራሮችና የፀጥታ አካላት ህይወት ሲጠፋ እንደነበር  የከተማዋ የአስተዳደርና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ምሥጋኑ ወጋሪ ተናግረዋል።

የከተማዋ ነዋሪ ህዝብ አካባቢውን ለመጠበቅ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በፈጠረው ቅንጅት የአካባቢው ሰላም መመለሱን አስረድተዋል።

የጸጥታ ችግር እንዲፈጠር ተሳትፈዋል ተብለው በከተማዋ ከተያዙት መካከል 41 ሰዎች ጉዳያቸው ተጣርቶ ለሕግ ለማቅረብ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው የከተማዋን ሰላም ለማስቀጠል  እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

ከነቀምቴ ከተማ ነዋሪዎች መካከል  አቶ ሽመልስ አምሳሉ በሰጡት አስተያየት በአካባቢው የህግ የበላይነትን ለማስከበር ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በመተባባር የድርሻቸውን እየተወጡ ቢገኙም  የተያዙ ሰዎች ለህግ እየቀረቡ ባለመሆኑ መስተካከል እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

አቶ ሙሉጌታ ቢራቱ የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ በበኩላቸው በነቀምቴ አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን የህዝቡ፣ አመራሩና ፀጥታው አካል ቅንጅት መጠናከር አለበት ብለዋል፡፡

የአካባቢያቸውን ሰላም ለመጠበቅ ከፀጥታው አካላት ጋር ያላቸውን ቅንጅት በማጠናከር የሕግ የበላይነት ለማረጋገጥ የሚሰራውን ስራ የሚደግፉ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የሻምቡ ከተማ ነዋሪ አቶ ደቻሣ ሻንቆ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም