የመረጃ፣ የደህንነትና የፀጥታ ተቋማት የኢኮኖሚ ወንጀሎችን፣ ሽብርተኝነትንና ህገ ወጥ ድርጊቶችን በጋራ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ተስማሙ

176

መስከረም 2/2012(ኢዜአ) የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ፣ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ እንዲሁም የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ እና የፋይናንስ ደህንነት መረጃ ማዕከል በአገሪቱ ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ የአምስትዮሽ ትብብራቸውን አጠናክረው ለመሥራት ተስማምተዋል፡፡

የመግባቢያ ሰነዱ የጋራ በሆኑ ተልዕኮዎቻቸው ላይ ይበልጥ ትኩረት ሰጥተው ተጋግዘውና ተናበው እንዲሰሩ ከማስቻሉም በላይ፤ ኮንትሮባንድና ህገወጥ የገንዝብ ዝውውርን እንዲሁም ህገወጥ የጦር መሳሪያ፣ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተጨማሪም በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብና ሽብርተኝነት እንዲሁም የጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎች ብዜትን በገንዘብ መርዳትንና የሳይበር ጥቃትን ለመከላከልና የተቀናጀ የኦፕሬሽን ሥራዎችን ለመምራት እንደሚያስችል የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ገልጿ።

በተያያዘ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የፋይናንስ ደህንነት መረጃ ማዕከልና የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የሶስትዮሽ ትብብራቸውን ለማጠናከር ከስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡

የመረጃና ደህንነት ተቋማቱ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረትን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብንና ሽብርተኝነትን እንዲሁም የጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎች ብዜትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር አስፈላጊ በመሆኑ የመግባቢያ ሰነዱን ተፈራርመዋል።

የስምምነት ሰነዱን የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል ኮሚሽነር ደመላሽ ገብረ ሚካኤል ፤ የፋይናንስ ደህንነት መረጃ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ በቀለ እንዲሁም የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ይግዛው ፈርመዋል።

የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የህዝብ ሰላምና ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲረጋገጥ ለማድረግ በአገሪቱ የሚገኙ የተለያዩ የመረጃ፣ የደህንነትና የፀጥታ ተቋማትን በማስተባበር ኦፕሬሽኖች ውጤታማ እንዲሆኑ ብቁ አመራር ሲሰጥ መቆየቱን ኢቢሲ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጠቅሶ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም