በበዓሉ ዋዜማና በዕለቱ በደረሰ የትራፊክ አደጋ የሁለት ሰዎች ህይወት ማለፉን የአዲስ ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ

64

አዲስ አበባ፣መስከረም 2/2013 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ በዘመን መለወጫ በዓልና በዋዜማው በደረሱ የትራፊክ አደጋዎች የሁለት ሰዎች ህይወት ማለፉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

በኮሚሽኑ ህዝብ ግንኙነት የሚዲያ ዲቪዥን ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ማርቆስ ታደሰ ትናንት የአዲስ ዓመት በዓልና በበዓሉ ዋዜማ በደረሱ የትራፊክ አደጋዎች የሁለት ሰዎች ህይወት ማለፉን ለኢዜአ ገልጸዋል።

ከአደጋዎቹ መካከል በነፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ሃና ማርያም አካባቢ ባጃጅ ተገልብጦ የባጃጁ ሹፌር ህይወት ማለፉን ተናግረዋል።

በባዓሉ ዋዜማ ስድስት ኪሎ አካባቢ የከተማ አውቶቢስ አንድ ሰው ገጭቶ ወዲያውኑ ህይወቱ ማለፉን ገልጸዋል።

በዓሉ ሰላማዊ ሆኖ እንዲከበር ከህብረተሰቡ ጋር በጋራ በመሆን አስፈላጊው ዝግጅት በመደረጉ ወንጀልና አደጋ መቀነሱን የገለጹት ዋና ኢንስፔክተር ማርቆስ ህብረተሰቡ ላሳየው ትብብር ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በሌላ በኩል ትናንት በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት በተለምዶ ፈረንሳይ ማዞሪያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሁለት ዛፎች ወድቀው በመኖሪያ ቤቶች ላይ ጉዳት አድርሰዋል።

አደጋው የደረሰው ከምሽቱ 2 ሰአት ገደማ በፈረንሳይ ማዞሪያ ወለተ እስራኤል ሰፈር አካባቢ ሲሆን በአንድ ቅጥር ግቢ ውስጥ በሚገኙ ቤቶች ላይ ጉዳት አድርሷል።

ዛፎቹ ረጅም እድሜ በማስቆጠራቸው በእለቱ ነፋስ ቀላቅሎ በጣለው ከባድ ዝናብ መውደቃቸውን የፈረንሳይና አካባቢው ፖሊስ ጣቢያ ሃላፊ ተወካይ ዋና ኢንስፔክተር ተረፈ ዘገየ ለኢዜአ ገልጸዋል። 

በወደቁት ዛፎችም በግቢ ውስጥ የሚገኝ ሰፊ መኖሪያ ቤት መጠነኛ ጉዳት ሲደርስበት ሶስት ቤቶች ከባድ እንዲሁም አራት ቤቶች መለስተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል ብለዋል።

ይሁን እንጂ በሰዎች ላይ ምንም አይነት ጉዳት አልደረሰም ነው ያሉት።

ፖሊስ ከህብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ በፍጥነት ቦታው ላይ በመድረስ አስፈላጊውን ማጣራት ማድረጉንም ዋና ኢንስፔክተር ተረፈ ገልጸዋል።

ዛፎቹ በአንድ የእንግዳ ማረፊያ (ገስት ሃውስ) ቅጥር ግቢ የሚገኙ ሲሆን የአካባቢው ነዋሪዎች "ዛፎቹ አርጅተዋል" ሊወድቁብን ይችላሉ በሚል ስጋት በተደጋጋሚ እንዲቆረጡላቸው መጠየቃቸውንም ገልጸውልናል።

የገስት ሐውሱ ባለቤት ጉዳት የደረሰባቸውን ቤቶች እንደሚገነቡና እንደሚጠግኑ በመግለጽ አሁንም የአደጋ ስጋት አለባቸው የሚባሉ ባህርዛፎችን እንዲቆረጡ ትዕዛዝ መሰጠቱን ዋና ኢንስፔክተሩ ገልጸዋል።

የአካባቢው ፖሊስም በቀጣይ አስፈላጊውን ክትትል በማድረግ እርምጃ እንደሚወሰድ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም