የአበበ ቢቂላ የኦሎምፒክ ድል መታሰቢያ ሩጫ ውድድር በሮም ተካሄደ

1436

አዲስ አበባ   መስከረም  1/2012 (ኢዜአ) አትሌት አበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ ሮጦ ያሸነፈበትን የማራቶን ውድድር በማስመልከት ትናንት በሮም የመታሰቢያ ሩጫ ውድድር ተካሄዷል። 

አትሌት አበበ ቢቂላ በ1952 ዓ.ም በጣሊያን መዲና ሮም በተካሄደ 17 ኛው የኦሊምፒክ ማራቶን ውድድር በባዶ እግሩ በመሮጥ 2 ሰዓት ከ15 ደቂቃ ከ16 ሴኮንድ በመግባት ታሪካዊ ድል ማስመዝገቡ ይታወሳል።

አትሌቱ በውድድሩ ያገኘው የወርቅ ሜዳሊያ አፍሪካ በኦሊምፒክ ውድድር ታሪክ ያገኘችው የመጀመሪያ መሆኑን ድሉን ይበልጥ ደማቅ እንዳረገውም የሚዘነጋ አይደለም።

የተመዘገበውን ድል አስመልክቶ የመታሰቢያ የሩጫ ውድድር ከ60 ዓመት በፊት አትሌት አበበ ቢቂላ በሮጠበት ተመሳሳይ ቀን፣ ቦታ እና ሰዓት በሮም "ተርሜ ዲ ካራካላ" ስቴዲየም የድሉ መታሰቢያ የሩጫ ውድድር መካሄዱን በሮም ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ውድድሩ "ACSI Italia Atletica" የአትሌቲክስ ክለብና በሮም የኢትዮጵያ ኤምባሲ ትብብር የተዘጋጀ ነው።

በመታሰቢያ ማራቶን ውድድሩ 106 ሯጮች የተሳተፉ ሲሆን በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በአንድ ላይ ሯጮችን መልቀቅ ባለመቻሉ የመጀመሪያው ሯጭ 195 ሜትር እንዲሁም ሌሎች ቀሪ 105 ሯጮች እያንዳንዳቸው 400 ሜትር እንዲሸፍኑ ሆኗል።


የሮም ከተማ ማህበረሰብ የተለያዩ የስፖርት ዘርፎች ኃላፊዎች በስታዲየሙ ተገኝተው ውድድሩን ተከታትለዋል።

በሮም የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተቀዳሚ ጉዳይ ፈፃሚ አቶ ሸጋው አባተ የመታሰቢያ በዓሉን በትብብር እና በድምቀት ለማዘጋጀት የተሳተፉ አካላትን አመስግነው ወደፊትም በትብብር እና በድምቀት ውድድሩ እንደሚካሄድ ቃል ገብተዋል።


ከውድድሩ በተጨማሪ የቡና አፈላል ስነ ስርዓት በቦታው የቀረበ ሲሆን የአትሌት አበበ ቢቂላ፣ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ሃብት እና መዳረሻዎች፣ የኢትዮጵያ ምድረ ቀደምትነትና የልማት እንቅስቃሴዎች የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ለታዳሚዎች መቅረባቸውን ከኤምባሲው የተገኘው መረጃ ያሳያል።

አትሌት አበበ በቂላ በሮምና በቶኪዮ ኦሊምፒክ ካስመዘገባቸው የማራቶን ድሎች ውጪ በ1960 ዓ.ም በሜክሲኮ በተካሄደው 19ኛው የኦሊምፒክ ውድድር በማራቶን ተሳትፎ 17 ኪሎ ሜትር ከሮጠ በኋላ እግሩ ላይ በነበረበት ሕመም ምክንያት ውድድሩን ማቋረጡ አይዘነጋም።

ውድድሩን ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ማሞ ወልዴ ማሸነፉም እንዲሁ።

በ1961 ዓ.ም አትሌት አበበ ከቶኪዮ ኦሊምፒክ መልስ ከአጼ ኃይለስላሴ በሽልማት ያገኘውን የቮልስ ዋገን መኪና አዲስ አበባ ውስጥ ሲያሽከረክር በደረሰበት አደጋ ከወገቡ በታች መንቀሳቀስ እንዳይችል አድርጎታል።

አትሌት አበበ በቂላ በ1961 ዓ.ም በ41 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።

አትሌት አበበ ከወይዘሮ የውብዳር ወልደጊዮርጊስ ጋር ትዳር መስርቶ አራት ልጆችን አፍርቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም