ቻይና በኢትዮጵያ የልማት ስራዎች ላይ ድጋፏን አጠናክራ ትቀጥላለች- አምባሳደር ታን ጄን

73

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 3/2012 (ኢዜአ) ቻይና በኢትዮጵያ የልማት ስራዎች ላይ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ታን ጄን ተናገሩ።

"የሸገር ፓርክ" ግማሽ ምዕተ ዓመትን ላስቆጠረው የሁለቱ ሀገራት ወዳጅነት ጥሩ ማሳያ መሆኑንም ነው የጠቆሙት።

ኢትዮጵያና ቻይና ይፋዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ከጀመሩ ሃምሳ ዓመታት ተቆጥሯል።

አሁን ላይ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ወደ ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ከመሸጋገሩም በላይ በአፍሪካ- ቻይና ወዳጅነት እንደ ጥሩ ማሳያ ይቆጠራል።

ባለፉት ሁለት የለውጥ ዓመታት ደግሞ ቻይና ለኢትዮጵያ የሰጠችውን ብድር ከመቀነስ ባለፈ በተለያዩ የልማት ስራዎች ላይ ግንባር ቀደም ተሳታፊ ሆናለች።

ዛሬ የተመረቀው የሸገር ፓርክ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ወጭው በቻይና መንግስት የተሸፈነ ነው።

በምረቃው ላይ የተገኙት በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር የኮሮናቫይረስ በቻይና በተከሰተበት የመጀመሪያዎቹ ጊዜያት ለቻይና ድጋፋቸውን ካሳዩ ቀዳሚ ሀገራት ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን ነው የተናገሩት።

ቻይናም በበኩሏ ኢትዮጵያ የኮሮቫይረስን ለመከላከል በምታደርገው ጥረት ውስጥ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገች መሆኑንም ገልጸዋል።

የተለያዩ የቻይና ኩባንያዎች የመመርመሪያ መሳሪያን ጨምሮ ሌሎች የኮሮናቫይረስ መከላከያ ግብዓቶችን በኢትዮጵያ ለማምረት ኢንቨስት ማድረጋቸውንም ነው የጠቆሙት።

የሁለቱ ሀገራት አጋርነት በሌሎች የልማት ስራዎች ላይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

አምባሳደሩ ሀገራቸው ኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍ ጥሩ የሚባል ሰራ ሰርታለችል ብለዋል።

የቪዲዮ ኮንፈረንሶችን ከማመቻቸት እንዲሁም የተለያዩ የድህንነት መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ድጋፍ መደረጉንም  ተናግረዋል።

የህክምና ቡድን ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ያለውን ልምድ እንዲያካፍል መደረጉን ገልጸዋል።

አሁን ላይ የቻይና ኩባንያዎች ማስክን ጨምሮ የመመርመሪያ መሳሪያዎችን በኢትዮጵያ ለማምረት ኢንቨስት እያደረጉ መሆኑንም ተናግረዋል።

ይህ ቅድሚያ የሰጠነው የጤና ዘርፍ ሲሆን በአጠቃላይ ቻይና የኢትዮጵያ ትልቋ የንግድና ኢንቨስትመንት ምንጭ ናት ብለዋል።

በመሆኑም በርካታ የቻይና ቱሪስቶች በቀጣይ ወደ ኢትዮጰያ እንደሚመጡ ያለቸውን እምነት በመግለጽ ሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ወደ ላቀ ከፍታ እንዲሸጋገር እንሰራለን ብለዋል።

የሸገር ፓርክ ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ላላው የሁለቱ ሀገራት ጥሩ ማሳያ መሆኑንም ነው አምባሳደሩ ያወሱት።

ፓርኩ በአሰራሩ ህዝብ ተኮር  በሆነ መልኩ የኢትዮጵያን ባህልና ስልጣኔ እንዲያሳይ ተደርጎ መገንባቱንም ተናግረዋል።

በመሆኑም በቀጣይ በርካታ የቻይና እና የሌሎች ሀገራት ቱሪስቶች ፓርኩን እንደሚጎበኙ ያላቸውን እምነት ከወዲሁ ተናግረዋል።

አሰራሩም ህዝብ ተኮር በመሆኑ በርካታ ቱሪስቶችን በመሳብ የአገልግሎት ዘርፉን ለማሳደግ ያግዛል ብለዋል። 

ፓርኩ የታላላቅ ስልጣኔ ባለቤት የሆኑትን የሁለቱን ሀገራት ማለትም የቻይናንና ኢትዮጵያን ግንኙነት የሚያጠናክር ነው።

አምባሳደር ታን ጄን ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ "መልካም አዲስ ዓመት" በማለት መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም