የሸገር ፓርክ የቻይናና ኢትዮጵያን ትብብር የበለጠ የሚያሳድግ ፕሮጀክት ነው

149

አዲስ አበባ፣ ጳግሜ 5/2012 (ኢዜአ) የሸገር ፓርክ የቻይናና ኢትዮጵያን ትብበር የበለጠ እንደሚያሳድግ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ታን ጂያን ገለጹ።

አምባሳደሩ በሸገር ፓርክ የወዳጅነት አደባባይ ምረቃ ስነስርአት ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ''ፓርኩ ለአዲስ አመት የተበረከተ ስጦታ ነው'' ብለዋል።

የሸገር ፓርክ ወዳጅነት አደባባይ የኢትዮጵያን ቀደምት ስልጣኔ፣ የባህል ስብጥርና አንድነት የሚያሳይ መሆኑንም መስክረዋል።

የፓርኩ ፕሮጀክት የወዳጅነት መሆኑን የገለጹት አምባሳደሩ፤ ''ይህም የቻይናና የኢትዮጵያን የቆየ ወዳጅነት የበለጠ ያሳድገዋል'' ብለዋል።

ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ወዳጅነት ጠንካራ፣ እስትራቴጂክና በትብብር ላይ የተመሰረተ መሆኑን አውስተዋል።

ለግማሽ ምዕተ ዓመት ያህል የዘለቀው የሁለቱ አገሮች ወዳጅነትና ትብብር የበለጠ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አምባሳደሩ አረጋግጠዋል።

የምጣኔ ሃብት እድገትን በማፋጠን፣ የአገልግሎት ዘርፉን በማስተዋወቅ፣ የስራ እድል በመፍጠር፣ ቱሪስት በመሳብና የገቢ ምንጭ በመሆን ፋይዳው የጎላ እንደሚሆን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከኮሮናቫይረስ በኋላ መጎብኘት ካለባቸው አገሮች አንዷ እንደምትሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የቻይና ዜጎች ከሚጎበኙት የቱሪስት መዳረሻዎች ውስጥ የሸገር ፓርክ አንዱ እንደሚሆንም ተናግረዋል።

''ቻይና ከአፍሪካ አገሮች ጋር በምጣኔ ሃብት፣ በማህበራዊና ፖለቲካ ዘርፎች እርስ በርስ በመደጋገፍ የምትሰራው ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል'' ብለዋል።

የሸገር ፓርክ የወዳጅነት አደባባይ የምረቃ ስነ-ስርአት ከሰአት በኋላም በተለያዩ መርሃ ግብሮች እንደሚቀጥል ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም