ስልጣንን አለአግባብ በመጠቀም የሰው ህይወት አጥፍተዋል የተባሉ ሶስት ግለሰቦች እንዲቀጡ ተወሰነባቸው

65
ጭሮ ሰኔ 6/2010 ስልጣንን አለአግባብ በመጠቀም የሰው ህይወት አጥፍተዋል የተባሉ ሶስት ግለሰቦች  በ20 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ መወሰኑን የምዕራብ ሐረርጌ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታወቀ ። የፍርድ ቤቱ ዳኛ አቶ አብዱልረሂም መሀመድ እንደገለፁት የቅጣት ውሳኔው የተላለፈባቸው ግለሰቦች በዞኑ  ቦኬ ወረዳ ይሰሩ የነበሩ  ሁለት የፖሊስ አባላትና የወረዳው የአስተዳደርና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ናቸው። ግለሰቦቹ በቦኬ ወረዳ ባለፈው ዓመት የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለማንሳት ለሰላማዊ ሰልፍ አደባባይ ከወጡ ሰዎች መካከል ስልጣንን አለአግባብ ተጠቅመው በጥይት የሶስት ሰዎችን ህይወት በማጥፋትና  ሁለት ሰዎችን ደግሞ በማቁሰል ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸው ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ በአቃቢ ህግ የቀርበለትን የሰነድና የሰው ማስረጃ ተንተርሶ ግራ ቀኙን በማከራከር  ከቆየ በኋላ ጥፋተኝነታቸውን በማረጋገጥ ዛሬ ባስቻለው ችሎት ሶስቱም ግለሰቦች እያንዳንዳቸው በ20 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ መወሰኑን ዳኛው አስታውቀዋል። አብዱራህማን አህመድ፣ መሐመድ ታጂር እና አህመድ ሀጂ የተባሉት እነዚህ ግለሰቦች ክሳቸውን እንዲከላከሉ እድሉ ቢሰጣቸውም ባለመቻላቸው የቅጣት ውሳኔ እንደጸናባቸውም አመልክተዋል፡፡ ዳኛው እንዳሉት በህዝብ ላይ ያልተገባ ተግባር የሚፈጽሙ አካላት ስልጣን  ህብረተሰቡን ማገልገያ እንጂ የመጨቆኛ  መሳርያ አለመሆኑን አውቀው ከተመሳሳይ ድርጊት  እንዲታቀቡ የሚያስተምር ውሳኔ ተላልፏል፡፡ የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የህግ ኦፊሰር አቶ ስንታየው ቶሎሳ በበኩላቸው ሕብረተሰቡ  ህገ-ወጥ  አመራሮችን ሳይፈራና ሳይታለል መሰል ችግሮችን ለህግ  በማቅረብ መብቱን ማስከበር እንዳለበት አሳስበዋል ፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም