አገራዊ ለውጡን አጠናክሮ ለማስቀጠል የህዝብ ምክር ቤቶች ድጋፍ ያስፈልጋል ተባለ

69
አዳማ  ሀምሌ 6/2010 በአገር አቀፍ ደረጃ እየመጣ ያለውን ለውጥና የዴሞክራሲ ጉዞ ከዳር ለማድረስ በየደረጃው የሚገኙ የህዝብ ምክር ቤቶች ድጋፍና ርብርብ ወሳኝ መሆኑን የጨፌ ኦሮሚያ አፈ ጉባኤ አቶ እሸቱ ደሴ ገለጹ። አገሪቱ አዲስ የለውጥ ምዕራፍ ውስጥ መግባቷን የገለጹት አቶ እሸቱ ለውጡ ውጤት እንዲኖረውና ፍሬ እንዲያፈራ መደገፍና እገዛ ማድረግ የሁሉም ድርሻ መሆኑን ተናግረዋል። የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ ለማጨናገፍ በየቦታው የሚታዩ እንቅስቃሴዎችን ማምከን የለውጥ ፈላጊ ህዝብና መንግስት ቀዳሚ አጀንዳና የጋራ ጥረት መሆን እንዳለበትም አፈ ጉባኤው አስገዝበዋል። " በየደረጃው የሚገኙ የህዝብ ምክር ቤቶች የለውጡ አካል በመሆን በየአካባቢውም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍንና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ከወጣቱና ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር በቅንጅትና በትብብር መስራት አለባቸው" ብለዋል። ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በተካሄደ ሰልፍ ላይ የደረሰው የቦምብ ጥቃት ለውጡን በማይፍልጉ ኃይሎች የተፈጸመ በመሆኑ ለቀጣይ ህዝብና መንግስት የበለጠ እንዲጠነቀቁ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል። አቶ እሸቱ እንዳሉት፣ በህዝቦች መካከል የታየው ዴሞክራሲያዊ አንድነት ይበልጥ በውጤት የታጀበ እንዲሆን ቅድሚያ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥና ሰላምን ለማስፈን ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይጠበቃል። "ለእዚህም ከክልል ጀምሮ በየደረጃው የሚገኙ የህዝብ ምክር ቤቶች ከሕብረተሰቡ ጋር መምከር፣ መወያየትና የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ ሁሉም ሰው የአካባቢውን ሰላምና ፀጥታ ነቅቶ እንዲጠብቅ ማድረግ አለባቸው" ሲሉ አመልክተዋል። ሕብረተሰቡ የሚፈልገው ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ በመሆኑ ይህን እውን ለማድረግ የህዝብ ምክር ቤቶች ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የጨፌ ኦሮሚያ አባልና በጨፌው የህግ፣  ፍትህና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ኢሳ ቦሩ ናቸው። " የህግ የበላይነት ሲኖር ፍትህ ይረጋገጣል፣ መልካም አስተዳደር ይሰፍናል" ያሉት ሰብሳቢው ይህን ለማድረግ አስተማማኝ ሰላም ማስፈን ቀዳሚ አጀንዳ አድርጎ መንቀሳቀስ እንደሚገባ አስታውቀዋል። " ለእዚህም በየደረጃው ካሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር በቅንጅት ለመስራት ዕቅድ አውጥተን እየተንቀሳቀስን እንገኛለን " ብለዋል። የሰላሙ ባለቤት ሕብረተሰቡ በመሆኑ አሁን በአገር ደረጃ እየተመዘገቡ ያሉ ሁሉን አቀፍ ለውጦች ለማስቀጠል በተደራጀ አግባብ ህዝቡን ለማንቀሳቀስ እንደሚሰሩም አመልክተዋል። ከእዚህ ጎን ለጎን የወጣቱን ንቃት የማጎልበትና ህዝባዊ መድረኮች በመፍጠር ለዘላቂ ሰላምና ልማት በትኩረት እንደሚሰሩ ነው የገለጹት። ወጣቱ በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የተረጋጋ ሰላም እንዲሰፍን በማድረግ በስኬት የታጀበውን ለውጥ የማስቀጠል ኃላፊነት በሚገባ አውቆ መወጣት እንዳለበትም አስገዝበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም