ኢትዮጵያዊቷ ዲፕሎማት በቪዛ ማጭበርበር በቁጥጥር ስር ዋሉ

102
አዲስ አበባ ሃምሌ 6/2010 በአሜሪካ ሎስአንጀለስ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክትል ኮንሱሌት ጀነራል የሆኑት ደስታ ወልደዮሐንስ ዴልካሶ ከቪዛ ማጭበርበር ወንጀል ጋር በተያያዘ በአሜሪካ ፌዴራል ፖሊስ መያዛቸውን የአገሪቱ ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታወቀ። ኢትዮጵያዊቷ ዲፕሎማት ከቪዛ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ በሶስት መዝገቦች ክስ ቀርቦባቸዋል። የአሜሪካ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ትናንት ባወጣው መግለጫ እንዳለው ዲፕሎማቷ ወንድማቸውና የትዳር ጓደኛው ጋብቻን በመደበቅ ሁለቱም ትዳር እንደሌላቸውና በእርሳቸው ድጋፍ የሚኖሩ ጥገኞች መሆናቸውን እንዲሁም የግለሰቦቹ የሆነውን ህፃን የራሳቸው ልጅ እንደሆነ በመግለፅ ዋሽተዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል። ዲፕሎማቷ በአውሮፓዊያኑ ሐምሌ 2016 የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ለአሜሪካ ኤምባሲ የቪዛ ጥያቄ እንዲሰጣቸው የሚጠይቅ ደብዳቤ አስፅፈዋል። ደብዳቤውም ዲፕሎማቷ በአሜሪካ ሎስአንጀለስ አብረዋቸው ከሚቆዩ የቤተሰባቸው አባላት ጋር የሚጓዙና እስከ ተልዕኳቸው ፍፃሜ ድረስም በዚያው እንደሚቆዩ ይገልፃል። የልጃቸውን ልጅ ልጃቸው መሆኑን የገለጹ ከመሆኑም በላይ ወንድማቸውንና የትዳር ጓደኛውን ደግሞ ጥገኞችና በእርሳቸው ድጋፍ የሚኖሩ የቤተሰባቸው አባል በማድረግ መግለፃቸውም በደብዳቤው ተመልክቷል። በዚሁ መረጃ መሰረትም የቤተሰቡ አባላት ኤ-1 የተሰኘው የዲፕሎማት ቪዛ ተሰጥቷቸው አሜሪካ መግባታቸውን የአገሪቱ ጠቅላይ አቃቤ ህግ በመግለጫው አመልክቷል። ከዚህ ዕለት ጀምሮም የወይዘሮ ደስታ ወንድምና ልጁ በአሜሪካ ዋሽንግተን ኖረዋል። ግለሰቧ በቀረበባቸው ክስ መሰረት ወንጀለኛ ሆነው ከተገኙ እስከ 30 ዓመት የሚደርስ የእስራት ቅጣት ሊፈረድባቸው ይችላል። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በጉዳዩ ላይ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም