የነጆ ሆስፒታል ኦክስጂን ማምረት ጀመረ

137

ነቀምቴ፣ ጳጉሜን 03/2012(ኢዜአ) በምዕራብ ወለጋ ዞን ነጆ ሆስፒታል ኦክስጂን የማምረት ሥራ መጀመሩን ሆስፒታሉ አስታወቀ፡፡

የሆስፒታሉ ሥራአስኪያጅ አቶ ኢሳያስ በንቲ እንድገለጹት በሆስፒታሉ አገልግሎት የጀመረው በቀን እስከ 68 ሲሊንደሮች ኦክስጂን የማምረት አቅም ያለው መሳሪያ በማመቻቸት ነው።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጨምሮ በአራቱ የወለጋ ዞኖች ለሚገኙ የጤና ተቋማት እና ህዝቦች አገልግሎት እንደሚሰጥም አስታውቀዋል፡፡

ለኦክሲጅን ማመረቻ መሳሪያውና ግንባታው ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደተደረገ ተመልክቷል።

በአሜሪካ የሚኖሩና  በፊት በሆስፒታሉ ሲሰሩ የነበሩ ሲስተር ኦብሴ ሉቦ  መንግሥታዊ ካልሆኑ ከአሲስት ኢንተርናሽናልና ሮተሪ ክለብ ድጋፍ በመጠየቅ ባገኙት ገንዘብ የኦክስጂን ማምረቻ መሣሪያውን ገዝተው ለሆስፒታሉ ማቅረባቸውን ሥራ እስኪያጁ አስረድተዋል፡፡

የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ኢፋ ተመስጌን በበኩላቸው የኦክስጂን ማምረቻ መሣሪያው በሆስፒታሉ ተቋቁሞ ኦክስጂን ማምረት መጀመር ቀደም ሲል ኦክስጂን አዲስ አበባ ሄዶ ለማስሞላት ይደርስባቸው የነበረውን  እንግልትና ወጪ እንዳስቀረላቸው ተናግረዋል።

ታመው ወደ ሆስፒታሉ የድንገተኛ የሕክምና ክፍል የሚመጡ ታማሚዎች መዳን እየቻሉ በኦክስጂን እጦት ምክንያት ህይወታቸው ያልፍ እንደነበር የተናገሩት ደግሞ የሆስፒታሉ ጠቅላላ ሐኪም ዶክተር አብዲ ለማ ናቸው።

አሁን ላይ ኦክስጂን በሆስፒታሉ ማምረት መጀመሩ የነበረውን ችግር በማቃለል ለምዕራብ ኦሮሚያና  ቤኒሻንጉል ጉሙዝ  አካባቢ ህዝቦች  መልካም አጋጣሚ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም