በዲፕሎማሲው መስክ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መስራት ያስፈልጋል

136

 አዲስ አበባ  ጳግሜ  2/2012  (ኢዜአ)ዲፕሎማቱ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች ለይቶ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ መንቀሳቀስ እንደሚገባው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አሳሰቡ።

ላለፉት 15 ቀናት ሲካሄድ የነበረው የአምባሳደሮችና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሥራ ኃላፊዎች ዓመታዊ ስብሰባ ዛሬ ተጠናቋል።

ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የተጠናቀቀው 2012 ዓመት በዓለም ላይ በአወንታዊና አሉታዊ ጎኑ የዲፕሎማሲ ሥራ የተፈተነበት ነበር።

ሚኒስትሩ በኢንቨስትመንት፣ በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ፣ በቱሪዝም፣ በፖለቲካና ሌሎች ዘርፎች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ዲፕሎማቱ ተግቶ መስራት እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል።

"በመላው ዓለም በሚደረግ የዲኘሎማሲ እንቅስቃሴ በመደመር እሳቤ የኢትዮጵያ ታላቅነት፣ ፍላጎትና ግብ  ነጸብራቅ መሆን ይገባቸዋል" ብለዋል።

ዲፕሎማቱ በስራው የኢትዮጵያን ሰላም፣ ብልጽግ፣ ዴሞክራሲንና ህብረብሔራዊ አንድነትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት መደገፍ እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

በቀጣይ ዓመት ዲፕሎማቶች በተመደቡበት አገር ነባራዊ ሁኔታውን ከግምት በማስገባት ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮችን በማስቀደም መስራት እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል።

እንደሚኒስትሩ ገለጻ ዲፕሎማቶች በተወከሉባቸው አገሮች ያሉትን ነባራዊ ሁኔታዎች አስቀድመው ከአገራዊ ጥቅም አንጻር በመገምገም መስራት ይኖርባቸዋል።

"ከውጭ ግንኙነት የትኩረት አቅጣጫ አኳያ በባህልና በተፈጥሮ ሃብት ከተሳሰሩት አገሮች ጋር ያለውን ግንኙነት ከፍ ማድረግ ያስፈልጋል" ሲሉም አመልክተዋል።

"የቀጠናው ተለዋዋጭነቱ እየጨመረ በመምጣቱ በዚህ በኩል ከፍተኛ ሥራ መስራት ይጠይቃል" ብለዋል ሚኒስትሩ።

በሚሲኦኖች ላይ እየታየ ያለው አሳፋሪ ተግባር ሊቆምና ሊታረም የሚገባው መሆኑንም አስገንዝበዋል።

እንደሚኒስትሩ ገለጻ ኢትዮጵያ የዓባይ ውሃን የምታለማው ለቅንጦት ሳይሆን የህይወት ጉዳይ በመሆኑና እንደ አገርና ህዝብ የመኖር ጥያቄ በማስገደዱ ነው።

ኢትዮጵያ በዓባይ ግድብ ላይ የያዘችውን የፍትሃዊነት አቋም አምባሳደሮች ለዓለም ማስረዳታቸውን እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።       

ኢትዮጵያ ያዘጋጀችውን የ10 ዓመት ዕቅድ ጠንቅቆ በማወቅ መንቀሳቀስ እንዳለባቸውም ነው አቶ ገዱ የገለጹት።

"ኮቪድ-19 በቱሪዝም ዘርፍ ጥሎት የሚያልፈው ጠባሳ ቢኖርም አገራት የአየር ክልሎቻቸውን እየከፈቱ በመሆኑ በንቃት መከታተል ያስፈልጋል" ብለዋል።

የሰው ኃይል ስምሪትን ማዘመን፣ ማብቃት፣ ስነ-ምግባር፣ ብሔራዊ ጥቅምን ማስቀደም፣ ወዳጅ አገሮችን ማፍራት ትኩረት የሚያሻቸው መሆኑም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም