የአማራና ኦሮሞ ህዝቦች አንድነት እንዲጠናከር በትብብር እንሰራለን- አቶ ሽመልስ አብዲሳ

99

ባህርዳር፣ ጳጉሜ /2012 (ኢዜአ) የአማራንና ኦሮሞን ህዝቦች ለዘመናት የዘለቀ ወንድማማችነትና አንድነትን በማጠናከር የኢትዮጵያ ብልፅግና እንዲሳካ በትብብር የሚሰሩ መሆናቸውን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።

የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ርዕስ መስተዳደር አቶ አሻድሊ ሃሰን በበኩላቸው የሰላምና ደህንነት ስራዎችን ከአማራ ክልል ጋር በትብብር እንሰራለን ብለዋል።

በአማራ ክልል ሰላም እንዲከበር የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ዛሬ በባህርዳር ከተማ እውቅና በተሰጠበት ስነ-ስርዓት  የተገኙት አቶ ሽመልስ አብዲሳ እንደተናገሩት የአማራና  ኦሮሞ ግንኙነት ረጅም ታሪክ ያለውና  በማንኛውም መንገድ ሊለያይ የማይችሉ ህዝቦች ናቸው።

የሁለቱ  ህዝቦች  አንድነት የኢትዮጵያን ቀጣይ እጣ ፈንታ በመወሰንና አንድነቷ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የጎላ ሚና አላቸው ብለዋል።

በ2012 ዓ.ም በርካታ የለውጥ ድሎች የተመዘገቡበት ቢሆንም ለውጡን የሚገዳደሩ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ማጋጠማቸውንም አውስተዋል።

"ለውጡ ኢትዮጵያን ከአደጋ በማውጣት አስቀጥሏል" ያሉት አቶ ሽመልስ በቀጣይም ይህው ለውጥ የሃገሪቱን ብልፅግና እንዲያረጋግጥ ብስለት ያለው አመራር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በእኩልነትና ወንድማማችነት የተመሰረተች ጠንካራ ሃገር መሆኗን ጠቅሰው፤ ይህ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና የህዝቦች ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በጋራ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

የሃገርን ብልፅግና ለማረጋገጥም ያለፈውን በይቅርታ መሻገር እንደሚገባ የገለጹት አቶ ሽመልስ ፤ለዚህም ትንንሽ ጉዳዮች ወደ ጎን በመተው ሃገርን ሊያሻግሩ በሚችሉ በታላላቅ ጉዳዮች ላይ አበክሮ መንቀሳቀስ ይገባል ብለዋል።

"ባለፉት ጊዜያት የህዝቦችን አንድነት የሚሸረሽሩ በርካታ አሜካላ እሾህ የሆኑ ዘሮች ተዘርተዋል" ያሉት ፕሬዚዳንቱ እነዚህ የሃገር ፀር የሆኑ እንቅፋቶችን ለቅሞ ለመጨረስ ጊዜ የሚወስድና በሆደ ሰፊነት ተጋግዞ መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ለዚህም በመደመር እሳቤ የሃገሪቱ ብልፅግና ይረጋገጣል፣ ኢትዮጵያም በህዝቦቿ አንድነት ደምቃ ትቀጥላለች ብለዋል።

ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚጥሩ ኃይሎች መቼም ቢሆን እንደማይሳካላቸውና ህልማቸውም በህዝቦች ጠንካራ አንድነት ከንቱ ሆኖ እንደሚቀር አስታውቀዋል።

የአማራና ኦሮሞ ህዝቦች ግንኙነት ከመሪዎች በላይ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያን አንድነት ለማስቀጠልም ከአማራ ክልል መንግስትና ህዝብ ጋር ጠንካራ አንድነት በመፍጠር በልማትና ሰላም ጉዳዮች በትብብር የሚሰሩ መሆናቸውን ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል።

ሌላው በስነ-ስርዓቱ የተገኙት የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ርዕስ መስተዳደር አቶ አሻድሊ ሃሰን በበኩላቸው  አማራና ቤንሻንጉል ጉምዝ  በባህልና ቋንቋ ተሳስረው  አብረው በጋራ የኖሩ ህዝቦች ናቸው ብለዋል።

የሁለቱን ህዝቦች አንድነት ያልወደዱ አካላት በየጊዜው በሚፈጥሩት አጀንዳ በመካከላቸው  ግጭት በመፍጠር ለጉዳት ሲያጋልጧቸው እንደቆዩ አውስተዋል።

በግጭቱ እጃቸውን አስገብተው ሲሰሩ የነበሩ ግለሰቦችንም በመለየት ለህግ እንዲቀርቡ መደረጉን አቶ አሻድሊ ገልጸዋል።

የብጥብጥ አጀንዳዎችን በጋራ በመመከትም የተፈናቀሉ ሰዎችን መልሶ ወደ አካባቢያቸው የማስፈር ስራ መከናወኑን አስታውቀዋል።

በቀጣይም የሰላምና ደህንነት ማስከበር  ስራዎችን ከአማራ ክልል ጋር በትብብር እንሰራለን ያሉት አቶ አሻድሊ የህዝቦቹ አንድነት እንዲጠናከርም እንዲሁ።

ይህም የህዝቦች አንድነት፣ ፍቅርና ብልፅግናን ለማሳካት እንደሚያግዝ ጠቅሰው፤ ለዚህም ብስለት ያለው አመራር በመስጠት የህዝቦችን የመኖር መዋስትና ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።  

በአቶ ሽመልስና አቶ አሻድሊ ለተመራው የሁለቱ ክልሎች  ልኡካን  የክልሉን ባህል የሚገልጽ አልባሳት ተበርክቶላቸዋል።

በስነ- ስርዓቱ  በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች፣ የጸጥታ አባላት፣ ወጣቶች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም