በሶማሌና ኦሮሚያ አዋሳኝ የተፈናቀሉ ዜጎችን በዘላቂነት ለመቋቋም የሚያስችል ድጋፍ እየተደረገ ነው

65
አዲስ አበባ ሀምሌ 6/2010 ከሱማሌና ከኦሮሚያ ክልሎች ወሰን አካባቢ በተፈጠረው ግጭት የተፈናቀሉ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚያስችል ድጋፍ እየተደረገ መሆኑ ተገለፀ። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እስካሁን ለተፈናቃዮቹ ባደረገው የእለት ድጋፍ ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ አውጥቷል። የአስተዳደሩ ከንቲባ ድሪባ ኩማና የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ጠይባ ሀሠን በክልሎቹ አዋሳኝ አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ለተፈናቀሉ 100 እማወራዎችና አባወራዎች የ10/90 የጋራ መኖሪያ ቤት ቁልፍ ዛሬ አስረክበዋል። የመኖሪያ ቤቱ የተሰጣቸው ከመፈናቀሉ ጋር በተያያዘ የከፋ የጤናና የስነ-ልቦና ችግር ላጋጠማቸው ዜጎች ነው። ከዚህም ሌላ ለ1 ሺህ 853 ግለሰቦች ደግሞ የቤት ግንባታ ለማካሄድ የሚያስችል የመሰረተ ድንጋይ የማስቀመጥ ስነ-ስርዓት በአዲስ አበባ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ተከናውኗል። የከተማዋ ከንቲባ ድሪባ ኩማ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት፤ መፈናቀሉ ካጋጠመ ወዲህ መስተዳደሩ ለተጎጂዎች የምግብ፣ የአልባሳት፣ የንጽህና መጠበቂያ እቃዎች አቅርቦት፣ የህክምናና የአምቡላንስ አገልግሎት በመስጠት የእለት ድጋፍ እያደረገ ይገኛል። እስካሁን ለተፈናቃዮቹ ከ2ነጥብ2 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉን የጠቀሱት ከንቲባው ተፈናቃዮቹን በዘላቂነት ለሟቋቋም ኮሚቴ የማደራጀት፣ እቅድ የማውጣት፣ የተፈናቃዮችን መረጃ የማደራጀትና የመለየት ተግባራትን እያከናወነ መሆኑንም አመልክተዋል። ተፈናቃዮቹን በዘላቂነት ለማቋቋምና የተረጋጋ ኑሮ እንዲመሩ ለማድረግ 23 ሄክታር መሬት ቦታ የመለየትና መረጣ የማካሄድ ስራ መሰራቱን ከንቲባው ገልፀዋል። በዚህ ቦታ ላይም ለ1ሺህ 853  አባወራዎችና እማወራዎችን የጋራ መኖሪያ ቤት ለመገንባት የሚያስችል ፕሮጀክት ተቀርፆ ዝግጅቱ መጠናቀቁን አቶ ድሪባ አስታውቀዋል። የቤቶቹን ግንባታ በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ለተፈናቃዮቹ ማስረከብ ይቻል ዘንድ የሚያስፈልገው በጀት ተመድቦ በቤቶች ግንባታ የተሻለ አፈጻጸም ያላቸው አንደኛ ደረጃ ኮንትራክተሮች መመረጣቸውን ተናግረዋል። ተጎጂዎቹ ከገጠማቸው የመፈናቀል አደጋ ተያይዞ ከደረሰባቸው የሞራልና የስነ-ልቦና ችግር በፍጥነት እንዲያገግሙ ህዝቡ የሚገባውን ድጋፍ እንዲያደርግላቸውም ከንቲባ ድሪባ ጠይቀዋል። እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች በተለይ በትምህርት፣ በጤናና በስራ እድል ፈጠራ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚመለከታቸው የክፍለ ከተማ ሥራ አስፈጻሚዎች በቅንጅት እንዲሰሩም አሳስበዋል። የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ጠይባ ሀሠን በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ የኦሮሚያ ክልል ተፈናቃዮቹን በዘላቂነት ለማቋቋም  ከፌዴራል መንግስት፣ ከህብረተሰቡና ከለጋሽ ድርጅቶችና ግለሰቦች ጋር በመቀናጀት የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል። በአሁኑ ወቅት ደግሞ የአዲስ አበባ አስተዳደር የቀድሞ የከተማዋ ነዋሪዎችን ተቀብሎ በዘላቂነት ለማቋቋም የተለያዩ ድጋፎች ማድረጉን ወይዘሮ ጠይባ አድንቀዋል። በተለይ መስተዳደሩ የሰው ልጅ መሰረታዊ ፍላጎት የሆነውን መጠለያ ገንብቶ ለተፈናቃዮች ለማስረከብ ቁርጠኛ አቋም ይዞ ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩ የሚበረታታ ነው ሲሉ አክለዋል። የተጀመረው የቤት ግንባታ ፕሮጀክት ተጠናክሮ ወደ ተሻለ ምዕራፍ እንደሚሸጋገርም ያላቸውም እምነት ገልጸዋል። የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ስንታየው ሀሠን በበኩላቸው ተፈናቃዮቹን በዘላቂነት ማቋቋም እንዲቻል ክፍለ ከተማው የ114 ነጥብ 476 ካሬ ሜትር የቦታ ዝግጅት ማከናወኑን ጠቁመዋል። ግንባታው በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ ተገቢውን የክትትልና የቁጥጥር ተግባራትን ያከናውናል፤ በሂደት ለሚያጋጥሙ ችግሮች አፋጣኝ መፍትሄ በማቅረብ የበኩሉን እንደሚወጣ ገልጸዋል። በሶማሌና ኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ተነስቶ በነበረው ግጭት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀላቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም