ሰዎች በህይወት እያሉ ለበጎ ሥራቸው እውቅና የመስጠት ባህል ሊጎለብት ይገባል ---ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ

101

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 1/2012(ኢዜአ) ሰዎች በህይወት እያሉ ለበጎ ሥራቸው እውቅና የመስጠት ባህል ሊጎለብት እንደሚገባ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ።

ስምንተኛው የበጎ ሰው ሽልማት መርሃ ግብር ዛሬ በኢንተርኮንቲነንታል ሆቴል ተካሄዷል።

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት በጎ ሥራ የሚሰሩ ጀግኖችን መዘከር፣ ስለ እነሱ መዘመርና እውቅና መስጠት በጣም አስፈላጊ ነገር ነው።

በኢትዮጵያ ሰዎች በህይወታቸው እያሉ መልካምና በጎ ሥራ የሚሰሩ ዜጎችን የማስታወስና እውቅና የመስጠት ባህል ሊዳብር እንደሚገባም ተናግረዋል።

በቅርብ ሆነው ለአገራቸው ትልቅ ሥራ እያከናወኑ ላሉ ሰዎች ተገቢውን እውቅና መስጠት እንደሚገባና ሰዎች መታወስ ያለባቸው ከሞቱ በኋላ ብቻ ሳይሆን በህይወት እያሉም እንደሆነ አመልክተዋል።

አድራጊ ሰዎች ሌሎች የእነሱን ተግባር እንዲከተሉና ወደፊት እንዲመጡ የሚያደርጉት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።

በተጨማሪም ዜጎች ለከፋ ችግር እንዳይጋለጡ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱም ገልጸዋል።

"በጎ ሥራ ማድረግና ባለ አቅም ሰዎችን መርዳት ለታሪክም አስተዋጽኦ እንደማድረግ ይቆጠራል" ብለዋል።

የበጎ ሰው ተሸላሚ ለሆኑት ግለሰቦችና ተቋማት እንኳን ደስ ያላችሁ ያሉት ፕሬዚዳንቷ ለመልካም ሥራቸው ክብር እንዳላቸውም አመልክተዋል።

"የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል በግንባር ቀደምትነት ለተሰለፉት የጤና ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች፣ ፈተናና ችግር ሳይበግራቸው እየሰሩ ላሉ የሕዳሴው ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ሠራተኞች ምስጋናዬ ከፍ ያለ ነው" ሲሉም ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ገልጸዋል።

ፕሬዚዳንቷ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን ለተወጡ ተቋማትም እውቅና የሰጡ ሲሆን ድርጅቶችም ብቻቸውን መበልጸግ ሳይሆን ማካፈል እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

አሁንም ኢትዮጵያ ችግሮቿንና ፈተናዎቿን እንድትሻገር የበጎ አድራጎት ሥራዎችና የበጎ አድራጊዎች ሚና ወሳኝ መሆኑንና ይሄም ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ጥሪ አቅርበዋል።

"አዲሱ ዓመት በ2012 ዓ.ም የታዩ ክፉ ተግባራት እንዳይደገሙ የምናደርግበት፣ አብሮነታችንን የምናጎለብትበትና ሁላችንም ለአገራችን ዘብ የምንቆምበት ሊሆን ይገባል" ብለዋል።

ዛሬ በተካሄደው 8ኛው የበጎ ሰው ሽልማት መርሃ ግብር ለስምንት ተሸላሚዎች ሽልማት ተበርክቷል።

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተቸገሩ ወገኖችን ለመርዳት መኖሪያ ቤቱን ወደ ጊዜያዊ መጠለያነት የቀየረው ወጣት ካሊድ ናስር፣ ለ100 ጊዜ ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የቦንድ ግዢ የፈጸሙት አቶ አስፋው ኪሮስ፣ ትውልድን በኢትዮጵያን በመቅረጽ አስተዋጽኦ ያደረገው የኢትዮጵያ ልጆች ቴሌቪዥን ጣቢያ መስራች አቶ ቢኒያም ከበደና በታላቁ የኢትየጵያ ሕዳሴ ገድብ ኢትዮጵያ ያላትን አቋም በማንጸበርቅ አስተዋጽኦ ያደረገው መሐመድ አል አሩሲ የበጎ ሰው ሽልማት ተሸላሚ ሆነዋል።

በዓባይ ወንዝ ላይ የተለያዩ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ፣ መጽሐፍ በመጻፍና የሕዳሴ ግድቡ ተደራዳሪ በመሆን አስተዋጽኦ እያደረጉ ያሉት ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ፣ ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ለዜጎች ድጋፍ በማድረግ ኢትዮ-ቴሌኮም፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል በግንባር ቀደምትነት ለተሰለፉት የሕክምና ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች እንዲሁም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ሠራተኞችም ሽልማቱ ተበክርቷል።

ተሸላሚዎቹ የተዘጋጀላቸውን በ" ጃ " (ጀግና-የሚለውን ለማመልክት) ፊደል ቅርጽ የተሰራ ዋንጫ ከኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እጅ ተቀብለዋል።

በስምንተኛው የበጎ ሰው ሽልማት መርሃ ግብር ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የዘንድሮ ስምንተኛ ዙር የበጎ ሰው ሽልማት በአሥር ዘርፎች ሽልማት ለመስጠት ታስቦ የነበረ ቢሆንም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የዘርፉ ሽልማት ቀርቶ ሁሉም ተሸላሚዎች ልዩ ተሸላሚ በሚል ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

የበጎ ሰው ሽልማት በበጎ ሰው ሽልማት ድርጅት መስራችና የቦርድ ሰብሳቢ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት አማካኝነት የሚካሄድ ነው።

የበጎ ሰው ሽልማት ላለፉት ሰባት ዓመታት በተለያዩ ዘርፎች ለኢትዮጵያ አስተዋጽኦ ላደረጉ ግለሰቦችና ተቋማት እውቅና ሲሰጥ ቆይቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም