የአትሌት አበበ ቢቂላ የመታሰቢያ ሩጫ ውድድር በሮም ሊካሄድ ነው

850

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ1/2012(ኢዜ) አትሌት አበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ ሮጦ ያሸነፈበትን የማራቶን ውድድር በማስመልከት ጳጉሜን 5 ቀን 2012 ዓ.ም በሮም የመታሰቢያ ሩጫ ውድድር ሊካሄድ መሆኑ ተገለጸ።

አትሌት አበበ ቢቂላ በ1952 ዓ.ም በጣልያን መዲና ሮም በተካሄደ 17 ኛው የኦሊምፒክ ማራቶን ውድድር በባዶ እግሩ በመሮጥ 2 ሰዓት ከ15 ደቂቃ ከ16 ሴኮንድ በመግባት ታሪካዊ ድል ማስመዝገቡ የሚታወስ ነው።

አትሌቱ በውድድሩ ያገኘው የወርቅ ሜዳሊያ አፍሪካ በኦሊምፒክ ውድድር ታሪክ ያገኝቸው የመጀመሪያ መሆኑን ድሉን ይበልጥ ደማቅ ያደረገ ነበር።


አትሌት አበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ ሩጦ ያስመዘገበውን ድል አስመልክቶ ጳጉሜን 5 ቀን 2012 ዓ.ም ከምሸቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ሮም በሚገኘው "በተርሜ ዲ ካራካላ ስታዲየም" የድሉ መታሰቢያ የሩጫ ውድድር እንደሚካሄድ ሮም ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።


የኮቪድ -19 ወረርሽኝ በደቀነው ስጋት እና ባሉ ክልከላዎች ምክንያት ብዙ ታዳሚ ወደ ስታዲየም መግባት እንደማይችልም ገልጿል።

የሩጫ ውድድሩ በቦታው፣ በቀኑ እና በሰዓቱ የሚካሄደው ጀግናው አትሌቱ ከ60 ዓመት በፊት ያስመዘገበውን ድል ለማሰብ መሆኑን ያስታወቀው ኤምባሲው፣ የሩጫ ውድድሩ በክልከላው መሰረት በተወሰኑ ታዳሚዎች እንደሚታሰብ አስታውቋል።

ኤምባሲው በጣልያን የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ በቦታው ተገኝተው የዝግጅቱ ተካፋይ እንዲሆኑ ማድረግ አለመቻሉን ገልጿል።


በቦታው ያልተገኙ ዜጎች በቀኑ እና በሰዓቱ የኢትዮጵያን የባህል ልብሶች በመልበስ ታሪኩን ለልጆቻቸውና ጓደኞቻቸው በማጋራት ባሉበት ሆነው የመታሰቢያ በዓሉን እንዲያከብሩ ኤምባሲው ጥሪውን አቅርቧል።

አትሌት አበበ ቢቂላ በሮም ካስመዘገበው ድል በተጨማሪ በ1956 ዓ.ም በጃፓን ቶኪዮ በተካሄደው 18ኛው የኦሊምፒክ ውድድር በማራቶን 2 ሰዓት ከ12 ደቂቃ ከ11 ሴኮንድ በማሸነፍ ተከታታይ ድል ማስመዘገቡ የሚታወስ ነው።

አትሌት አበበ ቢቂላ ነሐሴ 30 ቀን 1925 ዓ.ም በደብረብርሃን ከተማ አቅራቢያ በምትገኘው "ጃቶ" በተባለች ቦታ ነው ተወለደው።

ከልጅነቱ ጀምሮ በበገና ጨዋታ ጎበዝ የነበረው አትሌቱ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በክቡር ዘበኛ ተቀጥሮ በወታደርነት አገልግሏል።

በ1948 ዓ.ም በአውስትራሊያ በተካሄደው 16ኛው የሜልቦርን ኦሊምፒክ ውድድር ኢትዮጵያውን ወክለው በተሳተፉ አትሌቶች ተነሳስቶ በአገር ውስጥ በ5 እና 10 ሺህ ሜትር ውድድሮች ላይ በመካፈል ሩጫ መጀመሩን መረጃዎች ያመለክታሉ።

አትሌት አበበ በቂላ በሮምና በቶኪዮ ኦሊምፒክ ካስመዘገባቸው የማራቶን ድሎች ውጪ በ1960 ዓ.ም በሜክሲኮ በተካሄደው 19ኛው የኦሊምፒክ ውድድር በማራቶን ተሳትፎ 17 ኪሎ ሜትር ከሮጠ በኋላ እግሩ ላይ በነበረበት ሕመም ምክንያት ውድድሩን ማቋረጡ አይዘነጋም።

ውድድሩን ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አትሌት ማሞ ወልዴ ማሸነፉም እንዲሁ።

በ1961 ዓ.ም አትሌት አበበ ከቶኪዮ ኦሊምፒክ መልስ ከአጼ ኃይለስላሴ በሽልማት ያገኘውን የቮልስ ዋገን መኪና አዲስ አበባ ውስጥ ሲያሽከረክር በደረሰበት አደጋ ከወገቡ በታች መንቀሳቀስ እንዳይችል አድርጎታል።

አትሌት አበበ በቂላ በ1961 ዓ.ም በ41 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።

አትሌት አበበ ከወይዘሮ የውብዳር ወልደጊዮርጊስ ጋር በትዳር አራት ልጆችን አፍርቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም