ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የኮቪድ-19 መመርመሪያ ማዕከል ከፈተ

85

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜ 1/2012(ኢዜአ) የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የኮሮናቫይረስ መመርመሪያና ለህሙማን ህክምና የሚሰጥ ማዕከል ከፈተ።

ማዕከሉን የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በስፍራው ተገኝተው ትናንት መርቀው ከፍተውታል።

ማዕከሉ የኮቪድ-19 ህሙማን ህክምና የሚከታተሉበት 150 አልጋዎች መያዝ የሚችል ክፍልና የኮሮናቫይረስ የመመርመሪያ ክፍል እንዳለው ተገልጿል።

በቀን ከ 450 እስከ 500 ናሙናዎችን የመመርመር አቅም ያለው ማዕከሉ አገልግሎት ለማግኘት ወደ አዲስ አበባና አዋሳ ከተሞች ይደረግ የነበረው ጉዞ ያስቀራል ተብሏል።  

ማዕከሉ በወልቂጤ ከተማና አካባቢዋ ለሚኖሩ ከ5 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ህዝቦች አገልግሎት መስጠት እንደሚችል ተነግሯል።

የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ፋሪስ ደሊል እንደገለጹት፤ ማዕከሉ በከተማዋና አከባቢው የነበረውን የምርመራ አቅም ማነስ ያቃልላል።

በተለይም ማዕከሉ አውቶማቲክ የመመርመሪያ መሳሪያ ያለው መሆኑን ገልጸው፤ ''በቀጣይ በቀን እስከ 1 ሺህ 500 ናሙናዎችን የመመርመር አቅም ይኖረዋል'' ብለዋል።

የዩኒቨርሲቲው ሆስፒታል ለኅብረተሰቡ የሚሰጠው ሌሎች መደበኛ የጤና አገልግሎቶቹን ለማሻሻል ግብዓቶችን የማሟላት ሥራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ በበኩላቸው የተከፈተው ማዕከል የክልሉን የኮቪድ-19 የመመርመር አቅም ከፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

በደቡብ ክልል ሰባተኛ የመመርመሪያ ማዕከል ሆኖ የተከፈተው ይህ ማዕከል በአገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የመመርመሪያ ማዕከል ቁጥር ወደ 52 ከፍ የሚያደርግ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በተለይም ማዕከሉ አሁን ከጀመረበት የማኑዋል ምርመራ ወደ አውቶማቲም የምርመራ ሥራ ሲሸጋገር     ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ነው የተናገሩት።

''የዩኒቨርሲቲው ሆስፒታል ይህንን ብቻ ሳይሆን ሌሎችም መደበኛ የጤና አገልግሎቶችን በብቃት ለመሥራት የሚያስችል ግብዓት ድጋፍ ይደረጋል'' ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም