አሰራሮችን በማስተካከል አመራሩ ተጠያቂነት ያለው አካሄድ እንዲከተል ይደረጋል...ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች

61

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 29/2012(ኢዜአ) አሰራሮችን በማስተካከል አመራሩ ተጠያቂነት ያለው አካሄድ እንዲከተል እንደሚደረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

በቀጣዩ አመት በአዲስ አበባ ከተማ አንድ ሺህ በላይ ፕሮጀክቶች የሚጀመሩ ሲሆን 280 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጠር ምክትል ከንቲባዋ ጠቁመዋል።

ምክትል ከንቲባዋ ዛሬ ለአዲስ አበባ የብልጽግና ፓርቲ ቅርጫፍ ጽሕፈት ቤት ከፍተኛ አመራሮች ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ማጠናቀቂያ ላይ እንዳሉት፤ በከተማዋ የአመራሩን ብቃት በማሳደግ አሰራሮችን ማስተካከል ይገባል።

ከዚህ ውስጥም የአመራሩን ስምሪት በማስተካከል በከተማዋ ላይ ያሉ ፈተናዎችን መቋቋምና መፍታት የሚችል አሰራሮችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

አመራሩ ራሱን በውጤት የሚለካ፣ ብልሹ አሰራር ከማስቀረት አንፃር በጥንካሬ የሚሰራ መሆን እንዳለበትም ለአምስት ቀናት በተካሔደው ስልጠና ላይ በአጽንኦት መታየቱን አንስተዋል።

በመዲናዋ በተለይ በአሁኑ ሰዓት ከመሬት ወረራ ጋር የሚነሱ ችግሮችን መፍታትና መቋቋም የሚችል አመራር እንደሚያስፈልግም በስልጠናው መነሳቱን አመልክተዋል።

''አመራሩ ኃላፊነቱን ሳይወጣ የሚታዩ ችግሮችን ወደ ሕዝቡ ማውረድ የማይገባ ሲሆን ኃላፊነትን በመውሰድ ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ጉዳይም አጽንኦት ተሰጥቶታል'' ነው ያሉት።

በቀጣዩ አመት የከተማዋን ሰላምና ፀጥታ የማስጠበቅ እንዲሁም የሕግ የበላይነትን አክብሮ የማስከበር ተግባራት ትኩረት የሚሰጣቸው ጉዳዮች መሆናቸውንም በስልጠናው የመወያያ አጀንዳ እንደነበረም አመልክተዋል።

በከተማዋ ከአገልግሎት አሰጣጥና ከመልካም አስተዳደር ስራዎች ጋር በሚታዩ እንቅፋቶች ላይ በግልጽ ውይይት የተደረገ መሆኑንም ወይዘሮ አዳነች ተናግረዋል።

''የፓርቲ መስመር አንዱ መታገያና ማታገያ መሳሪያ ነው፤ በቀጣይም አመራሩ ጊዜያዊ ፈተናዎችን ለማለፍ የሚያስችሉ ወኔዎችን መታጠቅ አለበት'' ብለዋል።

ተመሳሳይ ስልጠና  በየደረጃው ላሉ አካላት እንደሚሰጥ አመልክተው፤ በቀጣይም ከከተማዋ ነዋሪዎች፣ ከወጣቶችና ባለሃብቶች ጋር ውይይቶች እንደሚካሔድም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም