በዞኑ እናቶች በቤት ውስጥ መውለዳቸው ለጉዳት እያጋለጣቸው መሆኑ ተገለጸ

68
ሁመራ ሐምሌ 6/2010 በትግራይ ምዕራባዊ ዞን እናቶች በቤት ውስጥ የመውለዱ ልማድ ባለመቅረቱ ለጉዳት እያጋለጣቸው መሆኑን የዞኑ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡ የጽህፈት ቤቱ አስተባባሪ አቶ ገብረ ብርሃን ብርሃነ ለኢዜአ እንዳሉት፣ለእናቶች የቅድመና ድህረ ወሊድ  ምርምራና ክትትል እየተደረገ  ቢሆንም በቤት ውስጥ እንዳይወልዱ የሚደረገውን ጥረት አሁንም ማስቀረት አልተቻለም። በአካባቢው ባህል ሆኖ የቆየውን እናቶች በቤት ውስጥ የመውለድ ልማድ  ለማስቀረት በየጊዜው ጥረት ቢደረግም  ለውጡ የሚፈለገውን ያህል አይደለም፡፡ "በህብረተሰባችን ውስጥ ገና ልንሰራበት የሚገባ ያልተቀረፈ የአመለካከት ችግር አለ፣ በቤት ውስጥ መውለድ እንደ ጎጂ ነገር ታይቶ እንዲቀር የሚደረገውን ጥረት ማስቀጠል ያስፈልጋል" ብለዋል። በዞኑ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 11 ወራት ውስጥ በወልቃይት፣ ጸገዴና ቃፍታ ሑመራ ወረዳዎች 19 እናቶችን በቤት ውስጥ በመውለድ ላይ እንዳሉ ህይወታቸው ማለፉን አመልክተዋል። በተለይም በጤና ባለሙያዎች ሊያገኙ የሚገባቸውን የደምና ሌሎች የህክምና አገልግሎት በማጣታቸው ለጉዳት የመጋለጣቸው ምክንያት መሆኑን ነው አስተባባሪው የተናገሩት። እንደ አስተባባሪው ገለጻ በቤት ውስጥ የሚወልዱ እናቶች በመድማት ምክንያት ተጎድተው ወደ ጤና ተቋማት መድረስ ቢችሉም ህይወታቸውን ለመታደግ አደጋች ነው፡፡ ባለፉት 11 ወራት ከወለዱ 9 ሺህ 841 እናቶች መካከል 843ቱ በቤት ውስጥ መውለዳቸውን ያመለከቱት አቶ ገብረ ብርሃን፣ "በዞኑ በቤት ውስጥ መውለድ ምን ያህል ስፋት እንዳለው ማሳያ ነው "ብለዋል። በዞኑ ከሚገኙ 79 ቀበሌዎች ውስጥ 16ቱ በቤት ውስጥ መውለድ ዜሮ ማድረግ እንደቻሉ ጠቁመው፤ በተለይ ሰቲት ሑመራና ቃፍታ ሑመራ ወረዳዎች በበጀት ዓመቱ የተቀናጀ ስራ  በመከናወኑ ለውጥ ማምጣታቸውን ጠቅሰዋል። በዞኑ የቃፍታ ሑመራ ወረዳ ነዋሪ  አቶ ብርሃኔ  መስፍን በሰጡት አስተያየት በአካባቢያቸው ባለሙያዎች በቅንጅት መስራት በመጀመራቸውና የአምቡላንስ አገልግሎት እንዲኖር በመደረጉ ለውጥ እየመጣ መሆኑን ተናግረዋል። ወይዘሮ አብርሄት ስዩም የተባሉት የዚሁ ወረዳ ነዋሪ በበኩላቸው፣ በአቅራቢያቸው ባሉ የጤና ባለሙያዎች በሚሰጣቸው የምክርና የግንዛቤ ትምህርት ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ እንደሚወልዱ ተናግረዋል። " በጤና ተቋም  መውለድ ለእናቶችም ሆነ ለህጻናት መልካም ነው"  ያሉት ወይዘሯዋ፣ በቤት ውስጥ መውለድ ለጉዳት  የሚያጋልጥ በመሆኑ እናቶች ወደ ጤና ተቋማት ሄደው እንዲወልዱ መክረዋል። "በአካባቢየችን እናቶች በጤና ተቋማት ውስጥ የመውለድ ፍላጎት እያሳዩ ናቸው፣ ቢሆንም የቆየውን ባህል አሁንም አልቀረም " ያሉት ደግሞ የፀገዴ ወረዳ ነዋሪ አቶ በረከት ክንፉ ናቸው፡፡ በቤት ውስጥ መውለድ አደገኛ መሆኑን በባለሙያዎች የግንዛቤ ትምህርት በመስጠት እየመጣ ያለውን የለውጥ ስራ ማጠናከር እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም