ወረፋ እየጠበቁ የሚገኙ ታካሚዎች እስከ መጪው ታህሳስ ድረስ አክሞ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው ተባለ

86
አዲስ አበባ ሀምሌ 6/2010 ሁሉንም ወረፋ የሚጠብቁ ታካሚዎችን  እስከ ታህሳስ 30 ቀን 2011 የቀዶ ህክምና ሰጥቶ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ። በአዲስ አበባ በሚገኙ ሆስፒታሎች የቀዶ ህክምና ወረፋ ከሚጠብቁ ከ11ሺህ በላይ ታካሚዎች መካከል ከ2 ሺህ 500 በላይ የሚሆኑት በአምስት ሳምንት አገልግሎት ማግኘታቸውንም አስታውቋል። በከተማዋ ያሉት ሆስፒታሎችና ከተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች ለከፍተኛ ህክምና በሪፈር የሚመጡ ታካሚዎች ቁጥር ባለመመጣጠኑ ታካሚዎቹ ለአላስፈላጊ እንግልትና ለጎንዮሽ ጉዳት እየተዳረጉ መሆኑ ይታወቃል። የአዲስ አበባ ነዋሪዋ ሙሉእመቤት ተሰማ ረዘም ላለ ዓመት የጨጓራ ህመም ምልክቶች ታይተውባት የተለያዩ ህክምናዎችን ብትክታተልም በቀላሉ ፈውስ ባለማግኘቷ እለት ተእለት ጨና ውስጥ መቆየቷን ትናገራለች። መጨረሻ ላይ በአካባቢዋ የሚገኝ አንድ የጤና ተቋም ጨጓራዋ ላይ ችግር እንዳለ በህክምና አረጋግጦ ወደ የካቲት 12 ሆስፒታል ሪፈር ተጽፎላት ህክምናዋን እንድትከታተል ይነገራታል። ሙሉእመቤት የካቲት 12 ሆስፒታል ህክምናዋን ለመጀመር የሚያስችል የኢንዶስኮፒ ምርመራ በቅድሚያ ማድረግ እንደሚገባት በተነገራት መሰረት ምርምራውን አድርጋ ውጤቱን ከአንድ ወር በኋላ ጠብቂ ተብላ ቀጠሮ እየጠበቀች ትገኝ ነበር። ከአንድ ወር በኋላም ባደረገችው የኢንዶስኮፒ ምርመራ ውጤት የጨጓራ እጢ እንዳለባት ይነገራትና ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የቀዶ ህክምና ማድረግ እንዳለባት ያሳስቧታል። ታማሚዋ ጥቁር አንበሳ እንደሄደችም ቀዶ ህክምና ለማድረግ በቂ አልጋ እንደሌለ ተነግሯት ላልተወሰነ ጊዜ ወረፋ እንድትጠብቅ መደረጓንም አክላለች። የቀዶ ህክምናዋን በወቅቱ ሳታደርግ አራት ወራትን ማስቆጠሯን ጠቁማ በዚህም በሽታዋ እየተባባሰ መምጣቱንም ተናግራለች። አሁን ግን ታካሚዋ በአዲስ አበባ ባሉ ሆስፒታሎች በተጀመሩት የዘመቻ ስራ የቀዶ ህክምናውን በቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በሶስት ቀናት ውስጥ እንደተደረገላት ትገልጻለች።  ሌላው ከመቀሌ ከተማ የመጣው ወጣት ይብራህ ካህሳይም እንደ ሙሉእመቤት በገጠመው የሆድ ህመም ህክምናውን በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሲከታተል ቆይቷል። የሆድ ህመሙ ያጋጠመው በስለት በመወጋቱ ምክንያት ቁስሉ ኢንፌክሽን አስከትሎ ቀዶ ህክምና ማድረግ እንዳለበት የሆስፒታሉ የህክምና ባለሙያዎች ቢነግሩትም ህክምናውን ለማድረግ ሁለት ዓመት ወረፋ እየጠበቀ እንደነበር ያስታውሳል። በአሁኑ ወቅት በቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ቀዶ ሕክምናውን ያደረገ በመሆኑ በመልካም ጤንነት ላይ እንደሆነ ነው የሚገልጸው። ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንደገለጸው አገልግሎቱ የተሰጠው በየሆስፒታሎች  የቀዶ ህክምና የሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች ወረፋን በመጠበቅ አገልግሎቱን በወቅቱ እያገኙ ባለመሆናቸው በቅብብሎሽ የህክምና አገልግሎት በመታገዝ ህክምናውን መስጠት በማስፈለጉ ነው። የቅብብሎሽ የህክምና አገልግሎት ማለት በየሆስፒታሎች ያሉ ታካሚዎች ቁጥር ከፍተኛ ሲሆን ጫና ወደ ሌላቸው ሆስፒታሎች ታካሚዎችን በማዘዋወር የሚሰጥ የህክምና አገልግሎት ነው። በዚህም በተከናወነው የቀዶ ህክምና አገልግሎት በአምስት ሳምንት  ግዜ ውስጥ ልክ እንደነ ሙሉእመቤትና ይብራህን ለመሰሉ በርካቶች ህክምናውን መስጠት መቻሉንም ነው የገለጸው። ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ከበደ ወርቁ እንዳሉት በአዲስ አበባ በሚገኙ  ሆስፒታሎች ከ11 ሺህ በላይ የሚሆኑ የቀዶ ህክምና ታካሚዎች ወረፋ በመጠበቅ ላይ ነበሩ። በዚህም ደግሞ ታካሚዎቹ አገልግሎቱን በወቅቱ ባለማግኘታቸው ለጎንዮሽና ተያያዥ ጉዳቶች እየተዳረጉ እንደነበር አንስተዋል። አሰራሩ ሚያዝያ ወር መጨረሻ መጀመሩን የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው እስከ ሰኔ መጨረሻ ድረስ ከ2 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ታካማዎች አገልግሎት መስጠት ተችሏል ነው ያሉት። ይህም ሆስፒታሎቹ እየሰጡት ካለው ጠቅላላ ህክምና በተጨማሪ ስፔሻላይዝድ ባደረጉበት ዘርፍ ቀዶ ህክናውን የሚያደርጉ ሲሆን እስከ ታህሳስ 30 ቀን 2011ዓ.ም ሁሉንም ወረፋ የሚጠብቁ ታካሚዎችን የቀዶ ህክምና ሰጥቶ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። አገልግሎቱ ሲሰጥ የህክምና ባለሙያ፣ የህክምና መሳሪያና የመድሃኒቶች ግብዓት በበቂ ሁኔታ በሟሟላት የተከናወነ ተግባር እንደሆነም አክለዋል። አሰራሩንም ወደ ሌሎች የአገሪቷ አካባቢዎች በማስጀመር  የጤና አገልግሎቱን ለሚሹ ታካሚዎች በወቅቱ ተደራሽ ለማድረግም እየተሰራ ነው ብለዋል። በዚህም ለክልል ጤና ቢሮዎች አገልግሎቱን እንዲጀምሩ በማድረግ በኩል በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረትም ሆስፒታሎችና ከተሞች የተለዩ በመሆኑ ቅርብ ለቅርብ ባሉ ሆስፒታሎች ታካሚዎችን በማዘዋወር ህክምናውን እንዲያገኙ ይደረጋል ነው ያሉት። አሰራሩ ተግባራዊ መደረጉ በወረፋ ምክንያት የህክምና አገልግሎት አሰጣጡ ላይ የሚያስከትለውን ጫና ከማስቀረቱም ባሻገር ፈጣን የህክምና አገልግሎት መስጠትን ባህል በማድረግ ረገድም ሚናው የጎላ እንደሆነ ነው ያብራሩት። በቀጣይም  በአገር አቀፍ ደረጃ  በቀዶ ህክምና ምክንያት ምንም ዓይነት ታካሚ ወረፋ መጠበቅ እንዳይኖርበት ለማስቻልም ያግዛል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም